የቬንዝዌላው ፕሬዝዳንት ማዱሮ እና ቢሊየነሩ ኢለን መስክ ሊደባደቡ ነው
ፕሬዝዳንት ማዱሮ በቴሌቪዥን ያቀረቡትን የእንደባደብ ጥያቄ ኢለን መስክ እንደተቀበለው አስታውቋል
ሁለቱ አካላት ላለፉት ጊዜያት ሀይለ ቃሎችን ሲወራወሩ ተስተውለዋል
የቬንዝዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ቢሊየነሩ ኢለን መስክ ለመደባደብ መስማማታቸው ተነገረ፡፡
ባለፉት ጊዜያት በማህበራዊ ትስስር ገጽ እና በመገናኛ ብዙሀን ሀይለ ቃላትን ሲለዋወጡ የሰነበቱት ሁለቱ አካላት ንግግራቸውን በድብድብ ለመደምደም ተስማምተዋል፡፡
ኒኮላስ ማዱሮ ባሰለፍነው እሁድ ለሶስተኛ ጊዜ የሰልጣን ዘመን ማሸነፋቸው ይፋ መደረጉን ተከትሎ በኤክስ ገጹ ላይ “አጭበርባሪ ፕሬዝዳንት” በሚል የገለጻቸው መስክ በስልጣን መቀጠል የሌለባቸው ፕሬዝዳንት ሲል ወርፏቸዋል ፡፡
ቀጥሎም የቬንዝዌላ ዜጎች የማዱሮን ሀውልት አፍርሰው የቀድሞውን የሀገሪቱን ፕሬዝደንት ሁጎ ቻቬዝ ሀውልት ሲተክሉ የሚያሳይ የተቀነባበር ተንቀሳቃሽ ምስል በገጹ ላይ ለጥፏል፡፡
ፕሬዝዳንቱ መስክ በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር አመጽ እና ብጥብጥን የመፈጥር አላማ ያለው ሀገራችንንም በስፔስ ሮኬቶቹ መውረር የሚፈልግ ዋነኛ ጠላታችን ነው ሲሉ ከሰወታል፡፡
ማዱሮ ሰኞ እለት በሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው “ከኔ ጋር መጣላት ትፈልጋለህ ቦታ እና ጊዜውን መርጠህ አሳውቀኝ እኔ የቻቬዝ እና ቦሊቫር ልጅ ነኝ” ሲሉ ዝተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የፕሬዝዳንቱን የይዋጣልን ጥያቄ መቀበሉን ያስታወቀው መስክ እኔ ካሸነፍኩ ማዱሮ ከስልጣን ላይ ይወርዳሉ ከተሸነፍኩ ደግሞ ፕሬዝዳንቱን በነጻ ወደ ማርስ የሽርሽር ጎዞ እጋብዛቸዋለሁ ብሏል፡፡
የስፔስ ኤክስ እና ቴስላ ዋና ስራ አስፈጻሚው ቢሊየነሩ ኢለን መስክ የተለያዩ ታዋቂ እና ተጽኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በመወረፍ እና ቡጢ ቢውዳደሩ እንደሚያሸንፋቸው በመፎከር ይታወቃል፡፡
ከዚህ ቀደም የፌስቡክን መስራች ማርክ ዙክርብርግ የቡጢ ውድድር ይዘጋጅልን እና እንተያይ የሚል ጥቄ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ ደግሞ ከቬንዝዌላው ፕሬዝዳንት ጋር ተፋጠዋል ሁለቱ አካላት እንዳሉት ፊት ለፊት ለመቧቀስ ይገናኛሉ ተብሎ አይጠበቅም ሆኖም ማዱሮ የሀገር መሪ ሆነው የእንቧቀስ ጥያቄ ማቅረባቸው መነጋገርያ ሆኗል፡፡
የቬንዝዌላ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ኒኮላስ ማዱሮ 51 በመቶ የመራጮችን ድምጽ በማግኝት ሀገሪቱን ለሶስተኛ ተከታታይ የስልጣን ዘመን ማስተዳደር የሚችሉበትን ይሁንታ ማገኝታቸውን አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሰኞ ጀምሮ ምርጫ ተጭበርብሯል ያሉ የሀገሪቱ ዜጎች በአደባባይ ተቃዎሟቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡