የሽንት ቀለም ስለጤናችን ምን ይናገራል?
አመጋገባችን እና የምንወስዳቸው መድሃኒቶች የሽንት ቀለም ለውጥ እንደሚያስከትሉ የሚገልጹ የጤና ባለሙያዎች፥ የተለያዩ የጤና ችግሮችንም ያሳያል ይላሉ
አንዳንድ ጊዜ የተለመደው የሽንት ቀለምም የጤና ችግርን ሊያመላክት እንደሚችል ባለሙያዎች ያነሳሉ
የህክምና ባለሙያዎች የሽንት ቀለም ለውጥን ከዚህ ቀደም ከውሃ ጥም ጋር ብቻ ያያይዙት ነበር።
በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች ግን የሽንት ቀለም ለውጥ የበርካታ የጤና ችግሮች ምልክት መሆኑን አሳይተዋል።
ውሃ የመሰለ ሽንት ውሃ በደንብ መጠጣትን ያሳያል የሚሉት ዶክተር ሌይላ ሃንቤክ፥ ደማቅ ቢጫ ቀለም ደግሞ ውሃ ጥምን እንደሚያመላክት ተናግረዋል።
ይህ መረጃ ተደጋግሞ የተነገረ ነው የሚሉት ዶክተር ሌይላ፥ አንዳንዴ ንጹህ (ውሃ ቀለም) ሽንት የጤና ችግርንም እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ቀን ውስጥ ከ6 እስከ 8 ብርጭቆ ውሃ መጠጣት ይመከራል፤ ከዚህ መጠን ያለፈ ውሃ መጠጣት የኤሌክትሮላይት መጠንን በመቀነስ የሽንት ቀለምን ከመለወጥ ባሻገር የሽንት ፊኛን ስራ ያበዛል ብለዋል።
ይህም የተለያዩ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል በመጥቀስም የሽንት ቀለም ለውጥ ሊያመላክት የሚችለውን የጤና ችግር እንዲህ ያብራራሉ፦
ውሃ ቀለም - ብዙ ውሃ መጠጣትን አልያም የጉበት ጤና ችግርን ያሳያል
ቀይ - የኩላሊት ጠጠር፣ የሽንት ፊኛ መጠን መጨመር፣
ቢጫ - የጉበት ህመም፣ የኬሞቴራፒ እና ተያያዥ መድሃኒቶች
አረንጓዴ ወይም ሰማያዊ- የቫይታሚን ቢ መብዛት፣ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን
ከአመጋገብ እና ከመድሃኒት ጋር በተያያዘ የሚፈጠር የሽንት ቀለም ለውጥ በአጭር ቀናት ውስጥ ወደቀደመ ቀለሙ ካልተመለ የጤና ባለሙያዎችን ማማከር ተገቢ መሆኑ ተገልጿል።
ሽንት ስንሸና የማቃጠል ስሜት ካለው፣ በተደጋጋሚ የመሽናት ፍላጎት እና የሆድ ህመምም የተለያዩ የጤና ችግሮች ምልክት ስለመሆናቸው ነው ዶክተር ሌይላ ሃንቤክ ያነሱት።