የዲ.አር ኮንጎው ፕሬዝዳንት ከኤም 23 አማጺያን ጋር ለድርድር ሊቀመጡ ነው
ከዚህ ቀደም ለድርድር ፈቃደኛ ያልነበሩት ፕሬዝዳንቱ ሁኔታዎች ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ አስገድደዋቸዋል

ከ12 አመታት በላይ ከመንግስት ጦር ጋር ውጊያ ላይ የሚገኘው የኤም 23 አማጺ ቡድን በምስራቃው ኮንጎ ይዞታውን እያጠናከረ ይገኛል
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ በሩዋንዳ ከሚደገፉት የኤም 23 አማፂያን ጋር ለመደራደር እያጤኑ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡
በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል በውጊያ ካሉት አማፂያን ጋር ለመደራደር ለረጅም ጊዜ ፈቃደኛ ሳይሆኑ የሰነበቱት ፕሬዝዳንቱ ተከታታይ ሽንፈትና የቀጠናው ድጋፍ እየቀነሰ መምጣት እንደገና እንዲያስቡ አስገድዷቸዋል እየተባለ ነው።
ኤም 23 መች እና እንዴት ተመሰረተ
ኤም 23 ወይም የማርች 23 ንቅናቄ በማዕድን በበለጸገው ምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከሚንቀሳቀሱ ከ100 በላይ ታጠቂ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው።
በሩዋንዳ እና በኡጋንዳ አዋሳኝ አካባቢዎች በሰሜን ኪቩ ግዛት ውስጥ የሚገኘው ታጣቂ ቡድን ከ8 ሺህ በላይ ተዋጊዎች እንዳሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
በ2012 የተመሰረተው ኤም 23 በቱትሲ ህዝቦች የሚመራው የሲኤንዲፒ ጦር ከመንግስት ጋር የገባው የ2009 ስምምነት አልተፈጸመም በሚል ነው ወደ ጫካ የገባው፡፡
ይህ ስምምነት የቱትሲ ተዋጊዎችን ወደ ጦር ሰራዊቱ ለማዋሃድ ፣ አናሳ የቱትሲ ጎሳዎችን ለመጠበቅ እና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚጠይቅ ነበር፡፡
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ታድያ ከሩዋንዳ ከሚያገኘው ድጋፍ እና በሚንቀሳቀስበት ምስራቃዊ ኮንጎ ያሉ ውድ ማዕድናትን በመሸጥ ራሱን እያጠናከረ ከ12 አመታት በላይ ከመንግስት ጦር ጋር እየተፋለመ ነው፡፡
ለድርድር የመቀመጥ ሀሳብ እና ውጤታማነት
100 ከሚደርሱ አማጺያን ጋር ባለፉት አመታት ውጊያ ላይ የሰነበተው የኮንጎ ጦር በውጊያ በመሰላቸት እና በሚደርስበት ተደጋጋሚ ሽንፈት የተነሳ ዕለት ዕለት ጦሩን በስፋት እየከዳ ይገኛል፡፡
ባለፉት ቅርብ አመታት እና 2025 ከገባ ጀምሮ ከኤም 23 አማጺያን ጠንከር ያለ መገዳደር የገጠመው የፕሬዝዳንት ቲሺሴኬዲ መንግስት በጫና ውስጥ ይገኛል፡፡
አስተዳደሩ የተለያዩ ሀገራትን ድጋፍ ቢጠይቅም ፣ በሩዋንዳ ላይ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያሳድር ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም በጦርነቱ ውሎ ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥን መመለከት አልቻለም፡፡
ይህን ተከትሎም ከዚህ ቀደም ከአማጽያኑ ጋር ለድርድር መቀመጥ የማይታሰብ መሆኑን ከመግለጽ ለዘብ በማለት ለድርድር ሊቀመጥ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተሰምቷል፡፡
ጎረቤት አንጎላ በመጪው ሳምንት የኮንጎ እና የኤም 23 ተደራዳሪዎች በዋና ከተማዋ ቀጥተኛ ድርድር ለማድረግ ይቀመጣሉ ስትል አስታውቃለች፡፡
የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ስለድርድሩ እስካሁን በይፋ ያስታወቀው ነገር ባይኖርም ሶስት የመንግስት ምንጮች ለማክሰኞው ድርድር የልዑካን ቡድን እንደሚላክ ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡
የኮንጎ ጦር እና አጋር ሃይሎች ለአማፂያኑ ግስጋሴ እየሰጡት ያለው ምላሽ በተዳከመበት በዚህ ወቅት የቀጠናው ሀገራት እና ባለብዙ ወገን ድርጅቶች መደራደር ብቸኛው መፍትሄ እንደሚሆን እየተናገሩ ነው፡፡
የኤም 23 ታጣቂ ቡድን በበኩሉ የኮንጎ መንግስት ለድርድር የማያሻማ ቁርጠኝነት እንዲያሳይ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈ የደቡብ እና የምስራቅ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስትሮች ጦርነቶችን ለማቆም በሚደረገው ጥረት ላይ ለመምከር የፊታችን ሰኞ ዚምቧቡዌ ሃራሬ ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዴሞክራቲክ ኮንጎ እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት እስካሁን ከ6 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የተመድ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በደቡብ እና ሰሜን ኪቩ በምስራቅ የሀገሪቱ ግዛቶች ከ4.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲፈናቀሉ በዚህ አመት ብቻ በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግጭት 400 ሺህ ሰዎች ተፈናቅለዋል።