የአየርመንገዱ እናት ኩባንያ ኤምሬትስ ግሩፕ ትርፍም ካለፈው አመት በ71 በመቶ ማደጉ ተገልጿል
የዱባዩ ኤምሬትስ አየርመንገድ 17.23 ቢሊየን ድርሃም (4 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር) ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።
አየርመንገዱ በፈረንጆቹ መጋቢት 31 2024 በተጠናቀቀው የበጀት አመቱ ያስመዘገበው ትርፍ ካለፈው አመት አንጻር የ63 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑንም ነው የገለጸው።
51.9 ሚሊየን መንገደኞችን ያጓጓዘው የኤምሬትስ አየርመንገድ ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ የአየር ትራንስፖርት ፍላጎቱ ዳግም እያንሰራራ መሆኑን የአየርመንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሼክ አህመድ ቢን ሳይድ ተናግረዋል።
የአየርመንገዱ እናት ኩባንያ ኤምሬትስ ግሩፕም አመታዊ ገቢ 137.3 ቢሊየን ድርሃም (37.4 ቢሊየን ዶላር) መድረሱ ነው የተገለጸው።
ኩባንያው ባለፈው አመት ያስመዘገበው ትርፍ በ71 በመቶ ማደጉ መገለጹንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ለኤምሬትስ አየርመንገድና ለኤምሬትስ ግሩፕ ትርፋማነት ማደግ የጎብኝዎች መዳረሻ የሆነችው ዱባይ ዋነኛዋ ምክንያት ናት።
ዱባይ በ2024 የመጀመሪያ ሩብ አመት ብቻ 5.18 ሚሊየን ጎብኝዎችን አስተናግዳለች። ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ11 በመቶ ጭማሪ አለው ተብሏል።
የኤምሬትስ አየርመንገድ ወደ 151 መዳረሻዎች የሚበር ሲሆን፥ ወደ 10 ከተሞች ደግሞ ጭነቶችን ብቻ ያመላልሳል።