የጃፓን አየርመንገድ አውሮፕላን በቶኪዮ በእሳት ተያይዟል
ከአስደንጋጩ ክስተት 379 መንገደኞችን እና የበረራ ቡድን አባላትን በአስደናቂ ሁኔታ ማትረፍ ተችሏል
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር የአደጋው መንስኤና የደረሰው ጉዳት በፍጥነት ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ አሳስበዋል
የጃፓን አየርመንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን ዛሬ በቶኪዮ ሃኔዳ አውሮፕላን ማረፊያ በእሳት ተያይዟል።
የሀገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኤንኤችኬ ክስተቱን በቀጥታ ሲያስተላልፈው የቆየ ሲሆን፥ ሁሉም መንገደኞች እና የበረራ ቡድኑ አባላት ከአደጋው ተርፈው መውጣታቸው ተዘግቧል።
12 የበረራ ቡድን አባላትን ጨምሮ 379 ሰዎችን ያሳፈረው አውሮፕላን በእሳት ቢያያዝም አንድም ሰው ህይወቱ ሳያልፍ ከእሳት አደጋው ማትረፍ መቻሉ የጃፓን አየርመንገድ የበረራ ባለሙያዎች ብርታትን ያሳያል በሚል እየተወደሰ ነው።
ኤርባስ 350 አውሮፕላኑ በእሳት ተያይዞ በጭስ የታፈኑ መንገደኞች ራሳቸውን ለማዳን ሲሯሯጡ የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች መውጣት ጅምረዋል።
367 መንገደኞችን ያሳፈረው የጃፓን አየርመንገድ አውሮፕላን መነሻው በሆካይዶ ደሴት ሺን ቺቶሴ ከተባለ አካባቢ እንደነበር ተገልጿል።
አውሮፕላኑ በትናንትናው እለት በደረሰው ርዕደ መሬት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ድጋፍ ከጫነና አምስት ሰዎችን አሳፍሮ ከነበረ የጃፓን ባህር ዘብ አውሮፕላን ጋር መጋጨቱም እየተነገረ ነው፤ በአነስተኛዋ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩት ሁሉም አምስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉም ቆየት ብለው የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ግን የአደጋውን መንስኤና የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ቡድን በፍጥነት እንዲቋቁም ከማዘዝ ውጭ እስካሁን ስለአደጋው መንስኤ ያሉት ነገር የለም ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
የቶኪዮ ሃኔዳ አውሮፕላን ማረፊያ የእሳት አደጋውን ተከትሎ በረራ ማቋረጡን አስታውቋል።
በትናንትናው እለት በተከሰተ ርዕደ መሬት 48 ዜጎቿን ያጣችው ቶኪዮ ዛሬ የሰው ህይወትን የሚቀጥፍ ከባድ አደጋ ቢደርስባትም በብልሃት ተወጥታው በንብረት ውድመት አልፎላታል።