ኤምሬትስ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ እለታዊ በረራዎችን ሊጀምር ነው
ከአሁን ቀደም በሳምንት አምስት ቀናትን ከአዲስ አበባ ዱባይ በረራዎችን ያደርግ እንደነበር የሚታወስ ነው
አየር መንገዱ ከጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም እለታዊ በረራዎቹን እንደሚጀምር አስታውቋል
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ንብረት የሆነው ኤምሬትስ አየር መንገድ ከጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ዕለታዊ በረራዎችን እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ከዚህ ቀደም በሳምንት አምስት ቀናትን ከአዲስ አበባ ዱባይ በረራዎችን ያደርግ እንደነበር ያስታወቀው አየር መንገዱ የበረራዎቹን ቁጥር ሊጨምር እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ከጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም ከአዲስ አበባና ወደ አዲስ አበባ እለታዊ በረራዎችን ማድረግ እጀምራለሁ ብሏል አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ፡፡
ይህ ወደ ዱባይ እና እየተበራከቱ ወደ መጡት መዳረሻዎቹ መጓዝ ለሚፈልጉ ደንበኞቹ የተሻለ የጉዞ አገልግሎት አማራጭን ለመስጠት እንደሚያስችለውም ነው ያስታወቀው፡፡
እ.ኤ.አ በ1985 የተመሰረተው ኤምሬትስ በአሁኑ ወቅት በዘመነኛ ኤርባስ እና ቦይንግ አውሮፕላኖች የበረራ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ 270 አውሮፕላኖችም አሉት፡፡
በአዲስ መልክ የሚጀምራቸው የአዲስ አበባ ዕለታዊ በረራዎችም በቦይንግ 777-300ER አውሮፕላን የሚደረጉ ናቸው፡፡
የአገልግሎት አድማሱ እየሰፋ መምጣቱን ያስታወቀው አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት በ6 አህጉራት 114 መዳረሻዎች እንዳሉት በመግለጫው ጠቁሟል፡፡ አጠቃላይ የመዳረሻዎቹ ቁጥር 157 ነው፡፡
ኤምሬትስ ከ172 ሃገራት የተውጣጡ በርካታ ሰራተኞች አሉት፡፡ እስከ ባለፈው ዓመት ወርሃ መጋቢት ድረስ የነበሩት ሰራተኞቹ ቁጥር 59 ሺ 519 እንደሆነም ከድረገጹ የተገኘው ይፋዊ መረጃ አመልክቷል፡፡