“ታሪካዊ ነው” የተባለለት የመጀመሪያው በረራ ከእስራኤል ወደ ሞሮኮ ተደረገ
እስራኤል እና ሞሮኮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማድረግ በቅርቡ መስማማታቸው የሚታወስ ነው
በረራው ቴል አቪቭ ከሚገኘው ቤን ጉሪዮን አየር ማረፊያ ወደ ራባት የተደረገ ሲሆን የአሜሪካ እና የእስራኤል መሪዎች አማካሪዎች በበረራው ተካተዋል ተብሏል
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ ጃሬድ ኩሽነርን እና የእስራኤል ብሔራዊ የደህነነት አማካሪ ሜይር ቤን ሻባትን የያዘ አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን ከቴላቪቭ ወደ ራባት አደርረገ፡፡
ከቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ የተደረገው በረራው ሀገራቱ በቅርቡ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ለመጀመር ከወሰኑ በኋለ የተደረገ የመጀመሪያው በረራ ነው ተብሏል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆቹ ታህሳስ 2020 እስራኤል እና ሞሮኮ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጀመራቸውን ማብሰራቸው የሚታወስ ነው፡፡
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጉዞው እጅግ ታሪካዊ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ቃል አቀባይ ኦፊር ገንድል ማን አውሮፕላኗ የእስራኤል አቪዬሽን አካዳሚ ንብረት እንደሆነች ገልጸዋል፡፡
በበረራው ከጃሬድ ኩሽነር እና ከሜይር ቤን ሻባት በተጨማሪ እስራኤላውያን እና አሜሪካውያን ተካተዋል፡፡
በሞሮኮ ሁለቱም ሀገራት ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቢሮዎችን ለመክፈትና ቀጥታ በረራ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ጨምሮ በርካታ ስምምነቶችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
በትራምፕ አነሳሽነት የቀረበው የአብርሃም የሰላም ስምምነት ቀደም ሲል ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ከባህሬን፣ ከሱዳን እና አሁን ደግሞ ከሞሮኮ ተፈርሟል፡፡
“ይህ መሆኑ የሚያስደስት ነው” ያሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒሚን ኔታንያሁ ከሌሎች ሀገራም ጋር የሚደረጉ የሰላም ስምምነቶች እንደሚኖሩ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራቱን በስም አልጠቀሱም፡፡