የተባበሩት አረብ ኢምሬት የኮፕ28 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን የፊታችን ህዳር ታስተናግዳለች
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለኮፕ28 ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገለጹ።
በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚመክረው ኮፕ28 ጉባኤ በተባበሩት አረብ ኢምሬት አዘጋጅነት የፊታችን ህዳር ይካሄዳል።
አረብ ኢምሬት ይህን ጉባኤ አይረሴ እና ለምድራችን ጠቃሚ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት እንዲሆን የኢንዱስትሪ ሚንስትሩን ዶክተር ሱልጣል አጃቢርን በፕሬዝዳንትነት መርጣለች።
በብራስልስ እየተካሄደ ባለው የአውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ ሀገራት መሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እንዳሉት ለኮፕ28 ጉባኤ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል ።
ፕሬዝዳንቱ ከአልዐይን ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ የፊታችን ህዳር በአረብ ኢምሬት አዘጋጅነት የሚካሄደው የአየር ንብረት ጉባኤ እየተጎዳ ላለው ዓለም የሚጠቅም ውሳኔ ይወሰንበታል ብዬ እጠብቃለሁ ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም "የአየር ንብረት ለውጥን እያየነው እና እየተጎዳንበት ነው፣ እኛም ጉዳቶችን ለመቀነስ እርምጃ መውሰድ አለብን" ብለዋል።
አውሮፓ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ መመዝገብ እና መቆጣጠር ጀምሯል ያሉት ፕሬዝድንት ማክሮን በ2030 የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንን በ55 በመቶ ለመቀነስ እቅድ ወጥቶ እየተተገበረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይሁንና የአውሮፓ ካርበን መቀነስ ብቻውን ዓለምን እንደማይቀይር ገልጸው ሌሎች ሰፋፊ ህዝብ እና ብዙ መጠን ያለው በካይ ጋዝ የሚለቁ አህጉራት ወደ ተግባር እንዲገቡ የኮፕ28 ጉባኤ ጥቅም ይኖረዋልም ብለዋል።