ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ አፍሪካ ህክምና ላይ ነበሩ
የእስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር አምብሮሴ ማንድቩሎ ድላሚኒ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በ52 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ቀደም ሲል ስዋዚላንድ ትባል የነበረችው የእስዋቲኒ ጠ/ሚኒስትር ከአራት ሳምንታት በፊት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ለመታከም ደቡብ አፍሪካ ወደ ሚገኝ ሆስፒታል አምርተው የነበረ ቢሆንም ህይወታቸውን ግን ማትረፍ አለመቻሉን የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
በፈረንጆቹ ሕዳር 16 ቀን በኮሮና የተያዙት ጠ/ሚኒስትሩ ጥሩ ስሜት ይሰማቸው እንደነበር ገልጸው ነበር፡፡ በወቅቱም ምክትላቸው ቴምባ ማሱኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩና የተረጋጋ ስሜት ላይ ናቸው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ጠ/ሚኒስትር አምብሮሴ ማንድቩሎ ድላሚኒ ከሕዳር 2018 ጀምሮ የእስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን እያገለገሉ ነበር ቢቢሲ እንደዘገበው፡፡ ወደ ስልጣኑ ከመምጣታቸው በፊት የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭው ኤም ቲኤን ውስጥ የሰሩ ሲሆን በባንክ ዘርፍም ለብዙ ዓመታት ሰርተዋል ተብሏል፡፡
በእስዋቲኒ 7ሺ ሰዎች በኮሮና ሲያዙ ከ 120 በላይ ሰዎች ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ከ72 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ሲሆኑ አንድ ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
የበለጸጉ ሀገራት የኮሮና ክትባትን ለማግኘት በእሽቅድድም ላይ የሚገኙ ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ አንዳንድ ሀገራት ክትባቱን መስጠት ጀምረዋል፡፡ አሜሪካም ፋይዘር የተሰኘውን ክትባት በቅርቡ መስጠት እንደምትጀምር አስታውቃለች፡፡