ክትባቶቹ በ636 ሃገሪቱ አካባቢዎች ይሰራጫሉ ተብሏል
አሜሪካ ከነገ ሰኞ ጀምሮ በፋይዘር የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ግዛቶች ማሰራጨት እንደምትጀምር አስታወቀች፡፡
ክትባቶቹ በቀጣዮቹ 24 ሰዓታት ውስጥ ተጓጉዘው ከ145 የተለያዩ አካባቢዎች ይደርሳሉ ያሉት የሃገሪቱ ጦር ጄነራል ጋስ ፔርና በመላ ሃገሪቱ በ636 ስፍራዎች እንደሚሰራጩ ገልጸዋል፡፡
የአገልግሎት ፈቃድን ያገኙት የፋይዘር ክትባቶች ከነገ በስቲያ ማክሰኞ በ425 ረቡዕ ደግሞ በ66 አካባቢዎች እንደሚደርሱ ይጠበቃል እንደ ሲቢኤስ ኒውስ ዘገባ፡፡
ክትባቶቹ ዩፒኤስ እና ፌዴክስ በተሰኙ የፖስታ የማጓጓዝ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ነው የሚሰራጩት፡፡
ቫይረሱ በመዋጋቱ ሂደት የፊት አውራሪነት ሚና ያላቸው የጤና ባለሙያዎች እና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ክትባቱን ቀድመው ከሚያገኙት መካከል ናቸው፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ ክትባቱን ከሁሉም ቀደም በአደባባይ እንዲወስዱ የሚያጠይቁ አካላትም ብቅ ብለዋል፡፡
መድሃኒት አምራቹ ፋይዘር 3 ሚሊዬን የኮሮና ክትባቶችን ለማምረት የሚያስችለውን ፍቃድ ከአሜሪካ ምግብና መድሃኒት አስተዳደር ማግኘቱ ይታወሳል፡፡
ከ16 ሚሊዬን የሚልቁ ሰዎች በቫይረሱ በተያዙባት አሜሪካ 300 ሺ ገደማ ሰዎች ሞተዋል፡፡
ትናንት ቅዳሜ ብቻ 219 ሺ 510 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ የ2 ሺ 368 ሰዎች ህይወት ማለፉን የጆንሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ወቅታዊ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡