ልዩልዩ
በሲኖፋርም የተዘጋጀው የኮሮና ክትባት 86 በመቶ ያህል ውጤታማ ስለመሆኑ ዩኤኢ አረጋገጠች
ክትባቱ ለድንገተኛ አደጋዎች ጥቅም ላይ እንዲውል ባሳለፍነው ወርሃ መስከረም ፈቃድ ማግኘቱ የሚታወስ ነው
ሊያስከትል የሚችለው ምንም ዓይነት ከባድ የደህንነት ስጋት እንደሌለም አስታውቃለች
በመጨረሻ የክሊኒካዊ የፍተሻ ሂደት ደረጃዎች ላይ የሚገኘው የኮሮና ክትባት 86 በመቶ ያህል ውጤታማ ስለመሆኑ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አረጋገጠች፡፡
ክትባቱ በብሄራዊው የቻይና የመድሃኒት አምራች ኩባንያ ሲኖፋርም የተዘጋጀ ነው፡፡
የክትባቱ የደረጃ 3 ክሊኒካዊ የፍተሻ ሂደቶች ባሳለፍነው ሃምሌ በዩኤኢ መጀመራቸውን ያስታወቀው የሃገሪቱ ጤና ሚኒስቴር የክትባቱን ውጤታማነት የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎችን አውጥቷል፡፡
ሚኒስቴሩ ክትባቱ ለድንገተኛ አደጋዎች ጥቅም ላይ እንዲውል ባሳለፍነው ወርሃ መስከረም ነበር ፈቃድ የሰጠው፡፡
አሁንም ሊያስከትል የሚችለው ምንም ዓይነት ከባድ የደህንነት ስጋት እንደሌለ አረጋግጧል እንደ ሃገሪቱ የዜና አገልግሎት (ዋም) ዘገባ፡፡
በክትባቱ የፍተሻ ሂደት በዩኤኢ የሚኖሩ 31 ሺ ገደማ በጎ ፍቃደኞች ተሳትፈዋል፡፡ ክትባቱ በይፋ እንዲመዘገብም ተደርጓል እንደ ገልፍ ኒውስ ዘገባ፡፡ ሆኖም የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም፡፡
በራሽያ ሰራሹ ስፑትኒክ-4 የኮሮና ክትባት ክሊኒካዊ የፍተሻ ሂደቶች የሚሳተፉ በጎ ፍቃደኞችም ከሰሞኑ በአቡዳቢ ሲፈለጉ ነበር፡፡
9 ሚሊዬን ገደማ ህዝብ ባላት ዩኤኢ 178 ሺ 837 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የ596 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡