በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ላይ የሚሰሩ አካለት ፌዴሬሽን መሰረቱ
ኢትዮጵያውያን ወደ ተለያዩ ሀገራት እየሄዱ ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ኤጄንሲዎች ደግሞ እነዚህን ሰራተኞች በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በመላክ ይታወቃሉ፡፡
ከዚህ ቀደምም የዜጎች ደህንነት አደጋ ላይ ሲወድቅ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁን ላይ ይህንን ለመካላከል ወደ ውጭ ሀገራት ዜጎችን የሚልኩ ማህበራት በአንድነት እንድሰሩ ሲጠየቁ ቆይተዋል፡፡
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም ዛሬ ዜጎችን ወደ ውጭ አገራት የሚልኩ ማህበራት ፌዴሬሽን መስርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት አገልግሎት ሰጭ ኤጄንሲዎች አሰሪ ማህበር፣ ዓለም አቀፍ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አሰሪ ማህበርና ህብረት ኢትዮጵያ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አሰሪ ማህበር ናቸው ፌዴርሽን የመሰረቱት፡፡
ማህበራቱ የመሰረቱት ፌዴሬሽን ስያሜም የኢትዮጵያ የውጭ አገር የስራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ይሰኛል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ዘርፍ ዘመናዊ የመረጃ ስርዓትን በመሳደግ፣ የሰራተኛን አቅም በማብቃት፣ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችንም መፍትሔ በመስጠት በጋራ መስራት ለሀገር ስኬት ይረዳል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ ማህበራቱ ወደ ፌዴሬሽን መምጣታቸው የተመቻቸ ስራ ለመስራት ያግዛል ብለዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት አቶ ነቢል መሀመድም ጥምረቱ የዜጎችን ጥቅምና ክብር የበለጠ ለማስጠበቅ እድል አለው ብለዋል፡፡
ሆኖም ዜጎችን በሀገወጥ መንገዶች ወደ ውጭ ሀገራት የሚልኩ አካላት ህግን መሠረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ ነው የተገለፀው፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ተወካይ ከኢትዮጵያ ጋር የሰራተኞች ስራ ስምምነት ለመፈራረም በዝግጅት ላይ ነን ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሳኡዲ አረቢያ አምባሳደር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ዜጎች በሳኡዲ አረቢያ በብዙ የስራ መስኮች ላይ እንዲሳተፉ እንሻለንበተለያዩ የሙያ አይነቶች የሰለጥኑ ዜጎችንም ለመላክ ንግግሮች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ያሉት የሰው ሃይል ማሰልጠኛ ተቋማት ለስራው በሚመጥን መልኩ ዜጎችን ማሰልጠን እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን ይህም በድጋሚ መታየት እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ስራ ፈላጊ ወጣቶችን በውጭ ሀገራት ስራ በማሰማራት ራሳቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙበትን አሰራር ማሳደግ ይገባልም ነው ተብሏል፡፡
ዜጎች ስልጠና አግኝተው ወደ ውጭ ሀገራት ከሄዱ ራሳቸውን ቤተሰባቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ ይገባል የተባለ ሲሆን ሁሉም ማህበራት ህግና ስርዓትን አክብረው እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቧል::