ከ450 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ
ባለፈው ጥቅምት ወር በወልዲያ ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች መካከል በተከሰተ ግጭት የተማሪዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ በሌሎች የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች አለመረጋጋቶች እየተስተዋሉ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ መደበኛ የመማር ማስተማር ተግባሩን ማከናወን ተስኖት ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን አሰናብቶ ግቢውን ሲዘጋ፣ መሰል እርምጃ ለመውሰድ በመንደርደር ላይ የሚገኙ ሌሎች ተቋማትም አሉ፡፡
ለችግሩ የቅርብ ምክኒያት በሆነው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ባሳለፍነው ሳምንት በተቀሰቀሰ ተጨማሪ ግጭት የአንድ ተማሪ ህይወት መጥፋቱ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ኃላፊነቱን ይወስዳል የተባለ አንድ ተማሪ ሐሙስ ታህሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋሉን አል-ዐይን አማርኛ ዜና መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡የዩኒቨርስቲውን ፕሬዝዳንት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) እንዳሉት ባለፉት ጥቂት ቀናት ግጭቱን በማስነሳት የተጠረጠሩ 14 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንድ መምህር መኖሩንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርስቲው ዋና ግቢ (ደሴ ካምፓስ) ትምህርቱን እንደሚከታተል የተገለጸው ተጠርጣሪው አብሮት የሚሠራ ሌላ ኃይል መኖር አለመኖሩም እየተጣራ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
በኮምቦልቻና ደሴ ካምፓሶቹ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተምረው ወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ በደሴ ካምፓሱ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያደናቅፉ ክስተቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢስተዋሉም፣ ክስተቶቹ ካምፓሱን ለመዝጋት የሚያስገድዱና ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ አይደሉም ሲሉም አክለዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከአጠቃላይ ሀገራዊ የፖለቲካው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች የስጋት እና የግጭት ቀጣና እንደሆኑ ዘልቀዋል፡፡
መወሰዱን የሳይንስ ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን በተቋማቱ በሚከሰቱ ችግሮች እና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ዛሬ ታህሳስ 26 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው መገለጫ ግጭት በመቀስቀስና በችግሩ በመሳተፍ በተወነጀሉ ከ450 በላይ ተማሪዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አስታወቋል፡፡
እርምጃው ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ ከትምህርት ገበታቸው እሰከማገድ የሚደርስ ቅጣት መሆኑን የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ሳሙሄል ክፍሌ ተናግረዋል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው ተማሪዎች መካከል ከ170 በላይ የሚሆኑት ከአንድ ዓመት እገዳ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ከተቋማቱ የተባረሩ ናቸው፡፡ ከ280 በላይ ተማሪዎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ግጭቶች እንዲባባሱና እልባት እንዳያገኙ አድርገዋል የተባሉ 10 መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ውላቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ የስራ እገዳን ጨምረ ከባድና ቀላል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
እርምጃው ቀጣይነት እንደሚኖረውም ዶ/ር ሳሙሄል ክፍሌ በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡