እናት ፓርቲ በአማራ ክልል የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪው እንደታሰረበት አስታወቀ
በምርጫ አዋጁ አንቀጽ 42 መሠረት ዕጩዎች በወንጀል ድርጊት እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ ያለመከሰስ መብት አላቸው
ግለሰቡ ሁከት በማስነሳት ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸውን ፖሊስ ገልጿል
እናት ፓርቲ ለአል ዐይን ዜና እንዳስታወቀው በአማራ ክልል የምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ደባይ ጥላት ግን ወረዳ፣ ቁይ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ የሆኑት አቶ ሐውልቱ ጸጋዬ ፈንታሁን ቁይ ፖሊስ ጣቢያ መጋቢት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡00 ጀምሮ ከታሰሩ ዛሬ 4ኛ ቀናቸውን ይዘዋል።
በምርጫ አዋጁ አንቀጽ 42 መሠረት ዕጩው ያለመከሰስ መብት ያላቸው እንደሆነ ቢታወቅም ፣ “የወረዳው ፖሊስ ህግ ጥሶ አስሮብናል እስሩ ፖለቲካዊ አነድምታ አለው” ብሏል ፓርቲው።
ፓርቲው ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁን የገለጸ ሲሆን ዕጩው “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ” ጠይቋል።
የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ንጉሴ ቀሬ በበኩላቸው አቶ ሐውልቱ ጸጋዬ ከመጋቢት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሁከት በማስነሳት ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“ተጠርጣሪው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ መሆናቸውን አናውቅም” ያሉት ዋና ኢንስፔክተር ንጉሴ ፣ አቶ ሐውልቱ የተያዙት ልዩ ቦታው ቁይ ተክለሀይማኖት ቤተክርስቲያን ውስጥ በተፈጸመ ሁከት እጃቸው አለበት በሚል ተጠርጥረው መሆኑንም ገልጸዋል። ግለሰቡ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውንም ነው ኢኒስፔክተሩ የገለጹት፡፡
በተፈጠረው ሁከት ሰዎች መጎዳታቸውን ገልጸው ፣ በዚህ ወንጀል ላይ ተጨማሪ ምርመራዎችን እና መረጃዎችን ለመሰብሰብ በተጠርጣሪ አቶ ሐውለቱ ጸጋዬ ላይ የ3 ቀን የፍርድ ቤት ቀነ ቀጠሮ ወስደው እየመረመሩ መሆኑንም የጽህፈት ቤት ሃላፊው ተናግረዋል።
ፍርድ ቤት የሰጠው ቀነ ቀጠሮ ሲያልቅ እና በሁከቱ ዙሪያ የተጀመረው ምርመራ ከተጠናቀቀ ፣ ተጠርጣሪው በዋስ ሊፈቱ እንደሚችሉም ዋና ኢንፔክተር ንጉሴ ገልጸዋል።