ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግድያዎችን ለማስቆም በመንግስት በኩል ችግሩን የሚመጥን ትኩረት አለመሰጠቱን ሁለት ፓርቲዎች ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትናንትናው እለት በጥቃት አድራሾች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢዜማና እናት ፓርቲዎች መንግስት ማንነትን መሰረት ላደረገ ግድያ በቂ ጥኩረት አልሰጠም አሉ
ኢዜማ እና እናት ፓርቲዎች ማንነትና መሰረት ያደረጉ ግድያዎች በፌደራል መንግስት በቂ ጥኩረት አልተሰጣቸው ብለዋል፡፡ፓርቲዎቹ የክልል እና የፌደራል የጸጥታ አደረጃጀት ከጎሳ እና ፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ መንገድ እንዲደራጅም ጠይቀዋል።
ኢዜማ እና እናት ፓርትዎች ከትናንት በስቲያ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግድያዎችን አስመልከተው መግለጫ አውጥተዋል።
ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች በፌደራል መንግስት ትኩረት እንዳልተሰጠው ገልጸዋል።
መሰል ጥቃቶችም ማስቆም የሚቻለው ሀላፊነት የሚሰማው እና ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ የጸጥታ መዋቅር ሲኖር ነው ያሉት ፓርቲዎቹ ወንጀል እና ግድያዎች ሲፈጸሙ ዝም ብሎ የሚያዩ ወይም ሀላፊነታቸውን ባልተወጡ አስፈጻሚዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቀዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ በቦኔ ቀበሌ በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ላይ ማንነት ላይ መሰረት ባደረገ ጥቃት የተረፉ ሰዎች ጥቃቱ ከመፈፀሙ በፊት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አካባቢው እንዲያስተዳድሩ ኃላፊነት ከተሰጣቸው የቀበሌና ወረዳ አስተዳዳሪዎች ማስፈራሪያ ይደርሷቸው ነበር ሲል ኢዜማ ገልጿል።
ይህም፣ ጥቃቱ ሆን ተብሎ እና ታቅዶበት ለመፈፀሙ እና እና የአካባቢው ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ተሳትፎ አንዳለበት ማሳያ ነውም ብሏል።
በተደጋጋሚ የተከሰቱት ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደሀገር እንዳንረጋጋ እና ዜጎች ከፍርሃት ተላቀው የዕለት ተእለት ሕይወታቸውን እንዳይመሩ እንቅፋት ከመሆኑም በተጨማሪ ከውጭ ለሚመጣብን ሉዓላዊነታችን እና የሀገር ደህንነታችን ላይ ላነጣጠረ አደጋ ተጋላጭ ማድረጉን ፓርቲዎቹ ተናግረዋል።
በመሆኑም የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት፣ ሰላም እና ደህንነት መጠበቅ አሁንም የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር በመሆኑ መንግስት ሃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በዜጎች ላይ ጥቃት እየተፈፀመባቸው ባሉ አካባቢዎች ያለው የመንግሥት መዋቅር በጥልቅ እንዲፈተሽ እና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ በኦሮሚያ፣ ምእራብ ወለጋ የተፈጸሙን ግድያ አውግዘው፤ ጥቃት አድራሾች ላይ የፌደራልና የክልል የጸጥታ ኃይሎች በቅንጅት የአጸፋ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በጥቃቱ 28 ሰዎች መገደላቸውንና 12 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ትናንት አስታውቋል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ከጥቃት አድራሾቹ ውስጥ በተወሰኑት ላይ እርምጃ መወሰዱንም ገልጾ ነበር፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ከጥቃቱ የተረፉ የአካባቢው ነዋሪዎች በትናንትናው እለት ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት የደህንነት ስጋት ውስጥ እንደሆኑና መንግስት እንዲደርስላቸው ተማጽነዋል፡፡