በእንግሊዝ ታራሚዎች ከእስር ቤት እየወጡ ስራ ሰርተው እንዲመለሱ እንዲፈቀድላቸው ሀሳብ ቀረበ
ታራሚዎች ከእስር ቤት ውጭ ራሳቸውን በሚያሻሽሉባቸው እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሳተፉ መፍቀድ ድጋሚ ወንጀል እንዳይፈጽሙ ያግዛል ተብሏል

እንግሊዝ በአውሮፓ ከፍተኛ የእስር ቤቶች መጨናነቅ ከሚታይባቸው ሀገራት ተርታ ትመደባለች
የቀድሞው የእንግሊዝ የፍትህ ሚኒስትር ሀገራቸው “የክፍት እስር ቤቶች ፖሊሲን” እንድትከተል ሀሳብ አቀረቡ፡፡
በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ እና ዌልስ የእሰረኞች የቅጣት ግምገማን የሚመሩት የቀድሞው የፍትህ ሚኒስትር ዴቪድ ጋውኬ እሰረኞች ከእስር ቤት ወጥተው እንዲማሩ እና እንዲሰሩ መፍቀድን ጨምሮ በተሃድሶ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቅጣት ውሳኔን ለመገምገም እና የእስር ቤቶች መጨናነቅን ለመቅረፍ በመንግስት በቀረበላቸው ጥሪ ወደ ስራ የተመለሱት ሚኒስትሩ፤ ስፔን በምትከተለው “የክፍት እስር ቤቶች ፖሊሲ” 25 በመቶ የሚሆኑ እስረኞች ቀን ቀን በከተሞች ውስጥ ስራ እንዲሰሩ እና ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ እድል እንደሚሰጣቸው ነው የገለጹት፡፡
ይህን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ለእስር ቤቶች የሚመደበውን በጀት ለመቆጠብ፣ እስረኞች የተሻለ ማህበረሰባዊ መስተጋብር እና ሀላፊነት እንዲሰማቸው ከማድረጉም ባለፈ ድጋሚ ወንጀል ላይ የመሳተፍ እድላቸውን እንደሚቀንሰውም አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሩ የሚመሩት የቅጣት አወሳሰን ግምገማ ተቋምም የቀላል ወንጀሎችን ቅጣት ለመሻር እና ማህበረሰባዊ ህጎችን ጠበቅ በማድረግ ለእስር የሚዳረጉ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ አቅዷል፡፡
መንግስት ቀደም ሲል ባወጣው የአስቸኳይ ጊዜ እቅድ የእስር ቤቶችን መጨናነቅ ለማስቀረት 5500 እስረኞችን ለመልቀቅ ሁኔታዎችን እያጤነ ይገኛል፡፡
የሀገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር ይህን የአስቸኳይ ጊዜ እቅድ ገቢራዊ በማድረግ በ2031 ከ14 ሺህ በላይ የእስር ቤት ክፍሎችን ነጻ ለማድረግ እቅድ ይዟል፡፡
ከአምስት ቀናት በፊት ይፋ የተደረገው የፍትህ ሚኒስቴር የቅርብ ጊዜ አሀዛዊ መረጃ በመላው እንግሊዝ እና ዌልስ የሚገኙ እስር ቤቶች ማስተናገድ የሚችሉት የታሳሪዎች ቁጥር 88,688 ሲሆን በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 85,877 እንደሚጠጋ አመላክቷል፡፡
የቀድሞው የፍትህ ሚኒስትር ዴቪድ ጋውኬ ያቀረቡት “የክፍት እስር ቤቶች ፖሊሲ” በመንግስት ምን ያህል ተቀባይነት እንደሚኖረው የታወቀ ነገር ባይኖርም የእቅዱን የመጨረሻ ሰነድ ለመንግስት የማቅረብ ሀሳብ እንዳላቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከፍተኛ የእስር ቤቶች መጨናነቅ ካለባቸው የአውሮፓ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው እንግሊዝ ከኢስቶኒያ እስር ቤቶችን በመከራየት የረጅም አመታት ፍርደኞችን ለመላክ እቅድ ስለመያዟ በቅርቡ መዘገቡ ይታወሳል፡፡