በእስር ቤቶቿ ውስጥ ራስን ማጥፋት የጨመረባት ጣሊያን አዲስ ህግ አወጣች
በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ እስር ቤቶች በ2024 65 እስረኞች ህይወታቸውን አጥፍተዋል
ጣሊያን ከፍተኛ የእስር ቤት መጨናነቅ ካለባቸው የአውሮፓ ሀገራት መካከል አንዷ ናት
በእስር ቤቶቿ ውስጥ ራሳቸውን የሚያጠፉ ታራሚዎች ቁጥር እየጨመረ የሚገኝባት ጣሊያን እስር ቤቶችን ለማሻሻል አዲስ ህግ አጸደቀች፡፡
ከፍተኛ የእሰረኞች መጨናነቅ በሚገኝባት ጣሊያን 206 እስር ቤቶች ያሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እስር ቤቶቹ ማስተናገድ ከሚችሉት በ10 ሺዎች ብልጫ ያለው ታራሚን እንደያዙ ሬውተርስ አስነብቧል፡፡
ባለፉት አምስት አመታት እስር ቤት ጠባቂዎች በእሰረኞች ላይ በሚያደርሱት ስቃይ እና ድብደባ እንዲሁም ተቋማቱ ባላቸው ደካማ መሰረተ ልማት እና መጨናነቅ ራሳቸውን የሚያጠፉ ዜጎች ቁጥር በተከታታይ እየጨመረ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ለእስር ቤቶቹ የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆን እስረኞች ማግኘት ከሚገባቸው መሰረታዊ አገልግሎት ጋር ሊጣጣም ባለመቻሉ ከፍተኛ ክፍተት ተፈጥሯል ነው የተባለው፡፡
በዚህ የተነሳም በሶስት ቀናት ልዩነት አንድ ታራሚ ራሱን የሚያጠፋ ሲሆን በእስር ቤት ጠባቂ ፖሊሶች ይደርሳል ከሚባለው ድብደባ እና ስቃይ ጋር በተገናኘ 13 የማረሚያ ቤት ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የጣሊያን ፓርላማ ዛሬ ያጸደቀው ህግ ተግባራዊ ሲደረግ የእስረኞችን እራስን ማጥፋት ፣ የእስር ቤቶችን መጨናነቅ እና አጠቃላይ አሰራሩን ለማሻሻል ያግዛል ተብሏል፡፡
አዲሱ ህግ ቀላል ወንጀል ሰርተው የታሰሩ ሰዎች የእስር ጊዚያቸው በማህበረሰብ አገልግሎት ተቀይሮላቸው ከእስር እንዲፈቱ ፣ ተጨማሪ በጀት ለእስር ቤቶች አስተዳደር እንዲያዝ እንዲሁም ታራሚዎች የሚዝናኑባቸው እና መሰረታዊ አገልግሎቶች የሚያገኙባቸው መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ያስችላል ነው የተባለው ፡፡
በአውሮፓ ከጣሊያን ባለፈ ፈረንሳይ ፣ ግሪክ ፣ ሮማኒያ እና ቆጵሮስ የእስር ቤት መጨናነቅ ካለባቸው ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በጣሊያን ሴቶች ፣ የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ከ20 – 49 እድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶች በብዛት ራሳቸውን ከሚያጠፉት መካከል ናቸው፡፡
ባለፈው 2023 አመት በአጠቃላይ 70 እስረኞች ራሳቸውን ሲያጠፉ ስምንተኛ ወሩ ላይ በሚገኘው 2024 አመት ደግሞ እስካሁን 65 ሰዎች በገዛ እጃቸው ነፍሳቸውን ማጥፋታቸው ተሰምቷል፡፡
የእስረኞች ቁጥር እንዲያሻቅብ የጆርጂያ ሜሎኒ አስተዳደር ያደረጋቸው የህግ ማሻሻያዎች ተጽእኖ ማድረጋቸው የተነገረ ሲሆን እነዚህ የህግ ማሻሻዎች ለተለያዩ ወንጀሎች የተቀመጡ ህጎች የእስር ቅጣት አመታትን ስለማራዘማቸው ነው የተሰማው፡፡
ከሶስት አመት በፊት ጀምሮ የእስረኞች ቁጥር የጨመረባት ጣሊያን በ2022 ሁለት ሺህ 61 ፣ በ2023 3970 አዳዲስ ታሳሪዎችን ወደ እስር ቤቶቿ ልካለች፡፡
206 እስር ቤቶች ያሏት ሀገሪቷ በአጠቃላይ ማስተናገድ የምትችለው የእስረኛ ቁጥር ከ51 ሺህ እምብዛም የተሻገረ ባይሆንም በአሁኑ ወቅት 61 ሺህ ታሳሪዎችን በማስተዳደር ላይ ትገኛለች፡፡