ኢስቶኒያ እስር ቤቶቿን በማከራየት ገቢ ለማግኘት ማቀዷን አስታወቀች
ለሀገሪቱ ካቢኔ የቀረበው እቅድ ከጸደቀ በአመት እስከ 33.5 ሚሊየን ዶላር ገቢ ያስገኛል ተብሏል
ብሪታንያ እና ስዊዲን የኢስቶኒያን እስር ቤቶች ለመከራየት አስቀድመው ጥያቄ አቅርበዋል
ኢስቶኒያ እስር ቤቶቿን በማከራየት ለበጀት ድጋፍ የሚሆን ገቢ ለማግኘት ማቀዷን አስታወቀች፡፡
የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ የእስር ቤቶች መጨናነቅ ላለባቸው ሀገራት እስር ቤቶችን ለማከራየት የሚያስችል ረቂቅ ለመንግስት ካቢኔ ቀርቧል፡፡
ሀሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ ከጸደቀ ኢስቶኒያ በአመት እስከ 33.5 ሚሊየን ዶላር ገቢ እንድታገኝ የሚስችላት መሆኑ ታውቋል፡፡
የፍትህ ሚንስትሯ ሊሳ ፓኮስታ በመላው አውሮፓ ወንጀል በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር ዝቅተኛ የወንጀል ምጣኔ ከሚገኝባቸው ጥቂት የቀጠናው ሀገራት መካከል ኢስቶኒያ አንዷ ናት ብለዋል፡፡
የ1.3 ሚሊየን ህዝብ ባለቤት የሆነችው ሀገር 3ሺህ የሚጠጉ የእስር ቤት አልጋዎች በተዘጉ እስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከሚገኙ እስር ቤቶች ውስጥ 50 በመቶዎቹ ብቻ እስረኞችእንደሚገኙባቸው ተነግሯል።
የፍትህ ሚንስትሯ ፓኮስታ ዝቅተኛ የወንጀል ምጣኔ ካለባቸው ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኖርዌይ ከአመታት በፊት እስር ቤቶቿን ለውጭ ሀገራት ታሳሪዎች ማከራየቷን ገልጸው በተመሳሳይ ዴንማርክ 300 እስረኞችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን እንዳስታወቀች ተናግረዋል፡፡
አክለውም በአሁኑ ወቅት ስዊድን እና ብሪታንያ የኢስቶኒያን እስር ቤቶች ለመከራየት ጥያቄ ማቅረባቸውን እንዲሁም ፊንላንድ 500 የሚጠጉ የእስር ቤት አልጋዎች እጥረት እንዳለባት ነው የገለጹት።
ለካቢኔ የቀረበው እቅድ ከጸደቀ ሀገሪቱን እየተፈተነ ለሚገኘው የበጀት እጥረት አኝዱ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የኢስቶኒያ አጠቃላይ የእዳ መጠን 8.25 ቢሊየን ዶላር ኘው፤ ይህም የሀገሪቷን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 19.6 በመቶ ሲሸፍን 3.4 በመቶ የበጀት ጉድለትን ፈጥሯል፡፡