ሱሰኛ ልጃቸውን ለመጠበቅ ቤታቸው ውስጥ የእስር ቤት ክፍል ያሰሩት እናት
በታይላንድ ከ1.1 ሚሊየን በላይ ሰዎች የአደንዛዥ እጽ ሲጠቀሙ ከዚህ ውስጥ ወደ 500 ሺህ የሚጠጉት ከ30 ቀናት 20 ቀናቶችን ዕጽ የሚጠቀሙ ናቸው
ታይላንዳዊቷ እናት ለ20 አመታት በቁማር እና አደንዛዥ ዕጽ ውስጥ የሚገኝ ልጃቸውን ለመጠበቅ ነው በመኖርያ ቤት ውስጥ የብረት እስር ቤት ያስገነቡት
ታይላንዳዊቷ አዛውንት እናት የአደንዛዥ ዕፅ እና የቁማር ሱሰኛ ልጃቸውን ከፈተና ለማራቅ በቤታቸው ውስጥ የብረት እስር ቤት ማሰራታቸው ተሰምቷል፡፡
ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ለዕፅ ሱሰኛ ልጃቸው እና ለራሳቸው ደህንነት ሲሰጉ የኖሩት የ64 አመቷ የታይላንድ ቡሪራም ግዛት ነዋሪ የራሳቸውን እና ልጃቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ ያልተለመደ እርምጃ ወስደዋል።
ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ከ42 አመት ጎልማሳ ልጃቸው ጋር ለአመታት እንደኖሩ የሚናገሩት እናት የልጃቸው የሱስ ደረጃ የፈጠረው ጭንቀት ለባለቤታቸው ህልፈት ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡
አዛውንቷ እናት ለአስርተ አመታት በሱስ ውስጥ የቆየው ልጃቸው ከራሱ አልፎ ለአካባቢው እና ለጎረቤት ስጋት በሆነ ደረጃ አመጸኛ መሆኑን ተከትሎ በተቋራጮችን እስር ቤት ከማስገንባታቸው በፊት በተለያዩ ጊዜያት በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 10 የሱስ ማገገሚያዎች ውስጥ ህክምና እንዲያገኝ ሙከራ ማደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ሁኔታዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ የልጃቸውም ሀይለኛነት ጨመረው ይባስ ብሎ ከአደንዛዥ እጽ ለመውጣት የጀመረው ቁማር ቁጡነቱን እና አመጸኛነቱን እያባባሰው እንደመጣ ነው የገለጹት፡፡
በዚህ የተነሳም በአንድ ወቅት በእርሳቸው እና በአካባቢው ሰው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በመፍራት ውሳኔው ላይ ሊደርሱ ችለዋል፡፡
በብረት አጥር በተሰራው ክፍል ውስጥ መታጠቢያ ፣ አልጋ እና ዋይፋይን የመሳሰሉ አስፈላጊ አግልግሎቶች የተሟሉለት ሲሆን፤ ምግብ ለማቅረብ የሚያስችል ክፍተት በማበጀት በተገቢው ሰአት ምግብ እንደሚያቀርቡለት እንዲሁም የ24 ሰአታት እንቅስቃሴውን በደህንነት ካሜራ እንደሚከታተሉት ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል፡፡
ስለ የእስር ቤት ክፍሉ ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ በስፍራው ተገኝቶ ባደረገው ጉብኝት ግለሰቧ በሰበአዊ መብት ጥሰት እና በህገወጥ እስራት ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችሉ ገልጿል፡፡
በሀገሪቱ ህግ መሰረት አንድን ሰው ያለፍቃዱ በህገወጥ መንገድ በእስር ማቆየት ከ3-15 አመት እስር የሚያስቀጣ ጥፋት ስለመሆኑ ተደንግጓል፡፡
ነገር ግን ለልጃቸው ለራሳቸው እና ለአካባቢያቸው ደህንነት በሚል የመጨረሻ ያሉትን መፍትሄ የተገበሩት እናት በእስር ይቀጣሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ፖሊስ እስር ቤቱን እንዲያስፈርሱ እና ለልጃቸው የተሻለ መፍትሄ እንደሚፈልግላቸው ቃል ገብቶላቸዋል፡፡
የአደንዛዥ ዕጽ ሱስ ከፍተኛ ራስ ምታት በሆነባት ታይላንድ ከአጠቃላይ ህዝቧ 1.1 ሚሊየን የሚሆኑት ከፍተኛ አደንዛዥ እጽ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ ወደ 500 ሺህ የሚጠጉት ከ30 ቀናት ውስጥ 20 ቀናቶችን አዘውትረው የሚጠቁሙ ናቸው ተብሏል፡፡