የጀርመን ደጋፊዎች ከስፔን ጋር የተደረገው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ እንዲደገም ጠየቁ
ደጋፊዎቹ ጨዋታውን የመሩት እንግሊዛዊ ከአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የዳኞች ዝርዝር እንዲሰረዙም ፊርማ በማሰባሰብ ላይ ናቸው
እስካሁን ከ36ሺ በላይ የበይነ መረብ ፊርማ ያሰባሰቡት ደጋፊዎቹ ጥያቄ ተቀባይነት የማግኝት እድሉ ምን ያህል ነው?
ባሳለፍነው አርብ በአዘጋጇ ሀገር ጀርመን እና ስፔን መካከል የተደረገው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ አድልኦ ተደርጎበታል ያሉ የጀርመን ደጋፊዎች ጨዋታው እንዲደገም ጠይቀዋል፡፡
የብሔራዊ ቡድኑ ደጋፊዎች እንግሊዛዊው ዳኛ አንቶኒ ታይለር እና የቫር ዳኞች በጨዋታው ለስፔን ያደላ ዳኝነት ሲሰጡ ስለነበር ከአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ዳኞች ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዙ ጠይቀዋል፡፡
2ለ1 በሆነ ውጤት በስፔን አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ በ18 የግብ ክልል ውስጥ ከጀማል ሙሴላ ተመቶ በቼልሲው ተከላካይ ማርክ ኩኩሬላ በእጅ የተነካው ኳስ ፍጹም ቅጣት ምት የሚያሰጥ እንደነበር ለማህበሩ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡
በጭማሪ ሰአት 23ተኛ ደቂቃ ላይ የኩኩሬላ እጅ ነክቶታል ተብሎ የተፈጠረው አወዛጋቢ አጋጣሚ ብዙዎች ፍጹም ቅጣት ምት እንደሚያሰጥ ቢጠብቁም እንግሊዛዊው ዳኛ አንቶኒ ታይለር ፔናሊቲ እንደማያሰጥ ወስነው ጨዋታውን አስቀጥለዋል፡፡
የአርቡን ጨዋታ ተከትሎ የስፖርቱ ቤተሰብ ለሁለት ተከፍሎ በመከራከር ላይ ይገኛል፡፡
እጅ ወደኳስ እና ኳስ ወደ እጅ የሚለውን የፍጹም ቅጣት ህግ ለመከራከሪያነት የሚያነሱ የስፖርት ተንታኞች ማርክ ኩኩሬላ አቋቋም በመጥቀስ እና እጁን ኳሷን ለመከላከል ሆን ብሎ አልተጠቀመም በሚል ፍጹም ቅጣት ምት እንደማያሰጥ ሲከራከሩ፤
ሌሎች ደግሞ ተጨዋቱ የሚገኝበት የእግርኳስ ሜዳው ክፍል በየትኛውም ሁኔታ ኳስ በእጅ ቢነካ ፍጹም ቅጣት ምት የሚሰጥ መሆኑን በመጥቀስ እየተከራከሩ ይገኛሉ፡፡
ይህን አስመልክቶ ለአውሮፓ የእግር ኳስ ማህበር ቅሬታቸውን ያስገቡት የጀርመን ደጋፊዎች ጨዋታው እንዲደገም እና እንግሊዊው ዳኛም ከዳኞች መዝገብ እንዲሰረዙ ጠይቀዋል፡፡
በነገው እለት በግማሽ ፍጻሜው ለዋንጫ ለማለፍ ከፈረንሳይ ጋር ጨዋታውን የምታከናውነው ስፔን ከጀረመን ጋር ድጋሚ የመጫወት እድሏ ጠባብ ነው፡፡
የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የደጋፊዎችን ቅሬታ ተቀብሎ ተገቢ ነው ብሎ ካሰበ በዳኛው ላይ እርምጃ ከመውሰድ የዘለለ ጨዋታውን ማስደገም የሚችልበት እድል እጅግ የመነመነ ነው፡፡
የስፔን እና ፈረንሳይ ጨዋታ አሸናፊ ከእንግሊዝ እና ኔዘርላንድ አሸናፊ ጋር በመጪው ሰኞ በሚካሄደው የዋንጫ ጨዋታ ላይ የሚፋለም ይሆናል፡፡