እንግሊዝ ለቀጣዩ ትውልድ ሲጋራን ልትከለክል መሆኑ ተሰማ
ሀገሪቱ በ2030 ከሲጋራ ማጨስ ነጻ ለመሆን እርምጃዎችን እየወሰድኩ ነው ብላለች
የሲጋራ እግድ እርምጃዎቹ በሸማች ወገን ላይ ያተኮሩ ናቸው ተብሏል
እንግሊዝ ለቀጣዩ ትውልድ ሲጋራን ልትከለክል መሆኑ ተሰማ።
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ የሚቀጥለው ትውልድ ሲጋራን መግዛት እንዳይችል የሚያደርግ እግድ ለማውጣት እያጤኑ ነው ተብሏል።
ጠቅላይ ሚንስትር ሱናክ ጸረ-ትንባሆ እርምጃ በመውሰድ ኒውዝላንድ ባለፈው ዓመት የወሰደችውን ፈለግ ለመከተል ማሰባቸው ተነግሯል።
ኒውዝላንድ በጣለችው እግድ በጎርጎሮሳዊያኑ ከጥር አንድ 2009 በኋላ ለተወለዱ ልጆች ሲጋራ መሸጥ አይቻልም።
"ብዙ ሰዎች ሲጋራ ማጨስ እንዲያቆሙ ማበረታታት እንፈልጋለን። ይህም በ2030 ከሲጋራ ማጨስ ነጻ ለመሆን ያለን ፍላጎት አካል ነው። ለዚህም ነው የአጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ እርምጃ እየወሰድን ያለነው" ሲሉ የብሪታንያ መንግስት ቃል አቀባይ ለሮይተር ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ መንግስት የታሰቡ እርምጃዎች በሸማች ወገን ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ውጥኑ በሚቀጥለው ዓመት ከሚደረገው ምርጫ በፊት ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ብሪታኒያ ባለፈው መጋቢት ወር ነጋዴዎች ደንበኛ ለመሳብ ይሰጡት የነበረውን ነጻ የሙከራ ኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ከልክላለች።
ከዚህ ውጭ የብሪታንያና ዌልስ ም/ቤቶች በሀምሌ ወር ለአንድ ጥቅም ብቻ የሚውሉ የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ መሳቢያዎችን ለአካባቢና ጤና ሲሉ እንዲታገዱ መንግስትን ጠይቀዋል።