ኮሮና እንግሊዝን ዳግም እገዳ እንድትጥል አስገደደ
ለሁለተኛ ጊዜ ያገረሸውን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሌሎች የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራትም እገዳዎችን እየጣሉ ነው
ሰዎች ለተፈቀደላቸው ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከቤታቸው እንዳይወጡ የ 4 ሳምንታት እገዳው ይከለክላል
በእንግሊዝ ለ 4 ሳምንታት የሚቆይ የእንቅስቃሴ እገዳ ሊጀመር ነው
ከኮሮናቫይረስ ዳግም ማገርሸት ጋር በተያያዘ ከሚቀጥለው ሀሙስ እለት ጀምሮ በእንግሊዝ ለ 4 ቀናት የእንቅስቃሴ እገዳ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለጸ፡፡
በእገዳው መጠጥ ቤቶች ፣ ሬስቶራንቶች ፣ጂሞች ፣ ብዙም አስፈላጊ ያልሆኑ መደብሮች እና ቤተ እምነቶች ዝግ የሚሆኑ ሲሆን ኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ትምህርት ቤቶች ግን ክፍት ሆነው እንደሚቆዩ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ነገ ሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ለምክር ቤት አባላት ማብራሪያ እንደሚሰጡ የሚጠበቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሰዎች ለገና መገናኘት እንዲችሉ አሁን እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለ 4 ሳምንታት ይቆያል የተባለው እግድ ውጤቱ በሚኒስትሮች እየተገመገመ ለተጨማሪ ቀናትም ሊራዘም እንደሚችል የሀገሪቱ የካቢኔ መስሪያ ቤት ሚኒስትር ማይክል ጎቪ ለስካይ ኒውስ ገልጸዋል፡፡
እገዳው ሰዎች ለተፈቀደላቸው ጉዳይ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ከቤታቸው እንዳይወጡ መከልከልን ያካትታል ተብሏል፡፡ በቤቱስጥ የሚደረግ ስብሰባም የእገዳው አካል ነው፡፡ በልዩ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር ሰርግ መደገስ የማይፈቀድ ሲሆን የቀብር ሥነ-ስርዓት ከ30 የማይበልጡ ሰዎች በሚገኙበት እንዲፈጸምም ያስገድዳል፡፡
ዩናይትድ ኪንግደም በትናንትናው ዕለት 21,915 አዲስ የኮሮና ተጠቂዎችን ሪፖርት ያደረገች ሲሆን ይህም ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ የሀገሪቱን ተጠቂዎች ቁጥር 1,011,660 አድርሷል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተጠቂዎችን በማስመዝገብ ዩኬ ከዩኤስ ፣ ህንድ ፣ ብራዚል ፣ ሩሲያ ፣ ፈረንሳይ ፣ ስፔን ፣ አርጄንቲና እና ኮሎምቢያ በመቀጠል ዘጠነኛዋ ሀገር ናት፡፡
የዩኬ አካላት የሆኑት ዌልስ እና ስኮትላንድ ቫይረሱ በብዛት ወደተሰራጨበት ወደ እንግሊዝ (ኤንግላንድ) ዜጎቻቸው እንዳይሄዱ እንዲሁም ሰዎች ከዚያ እንዳይመጡባቸው በማገድ እና በመምከር ላይ ናቸው፡፡
ፈረንሳይ ፣ ቤልጂየም እና ጀርመንን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ የአውሮፓ ሀገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የተለያዩ እገዳዎችን ጥለዋል በመጣልም ላይ ናቸው፡፡
እስካሁን በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ46.4 ሚሊዮን በላይ ሲሆን ከነዚህም ከ33.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሲያገግሙ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡