አሜሪካ ኮሮናን መቆጣጠር እንደማትችል ከፍተኛ የኋይት ሀውስ ባለሥልጣን ገለጹ
በሀገሪቱ ቫይረሱ ህይወታቸውን የነጠቃቸው ሰዎች ቁጥር 225,000 ገደማ ደርሷል
የዴሞክራቶቹ እጩ ጆ ባይደን ከኮሮና ጋር በተያያዘ “ኋይት ሀውስ የሽንፈት ነጭ ባንዲራ እያውለበለበ ነው” ብለዋል
አሜሪካ ኮሮናን መቆጣጠር እንደማትችል ከፍተኛ የኋይት ሀውስ ባለሥልጣን ገለጹ
የትራምፕ ከፍተኛ ረዳት እና የኋይት ሀውስ የሰራተኞች ኃላፊ የሆኑት ማርክ ሜዶውስ ትናንት በሰጡት አስተያየት አሜሪካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መቆጣጠር እንደተሳናት ገልጸዋል፡፡
“ወረርሽኙን አንቆጣጠርም ፡፡ ክትባቶችን ፣ ህክምናዎችን እና ሌሎች የማስታገሻ አማራጮችን የምናገኝበትን ሁኔታ እንቆጣጠራለን” ብለዋል ሜዶውስ በሰጡት አስተያየት፡፡
ኃላፊው ይህን ያሉት ቫይረሱ በመላው አሜሪካ በፍጥነት እየተሰራጨ ቢገኝም የትራምፕ አስተዳደር ወረርሽኙን ለመቆጣጠር መደረግ ያለባቸውን የህክምና ባለሙያዎች ምክረ-ሀሳቦች እያጣጣሉ በሚገኙበት ወቅት ነው፡፡
የማርክ ሜዶውስን ሀሳብ ተከትሎ “ኋይት ሀውስ የሽንፈት ነጭ ባንዲራ እያውለበለበ ነው” ሲሉ የዴሞክራቶች እጩ ጆ ባይደን ገልጸዋል፡፡ የሜዶውስ አስተያየት “የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካን ህዝብ የመጠበቅ መሰረታዊ ግዴታውን መወጣት እንዳልቻለ ያሳያል” ነው ያሉት ባይደን፡፡
በሀገሪቱ በስፋት እየተሰራጨ የሚገኘው ቫይረሱ 225,000 ያህል ሰዎችን ወደ ሞት ሸኝቷል፡፡
በኋይት ሀውስ እንኳን ቫይረሱ ለሁለተኛ ዙር በወረርሽኝ መልክ እየተከሰተ እንደሆነ የሲኤንኤን ዘገባ ያመለክታል፡፡ ባለፉት ቀናት በምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ዙሪያ የሚገኙ 5 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝተቶባቸዋል፡፡
አሜሪካ ወረርሽኙን “በቁጥጥር ስር ማዋል የተሳናት ለምንድነው” በሚል ከሲኤንኤን ጋዜጠኛ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ፣ “ምክንያቱም ልክ እንደ ጉንፋን ሁሉ ተላላፊ ቫይረስ ነው” በማለት በዚህም ሳቢያ ቫይረሱን መቆጣጠር ሊሳካ የሚችል ግብ እንዳልሆነ ሜዶውስ አንስተዋል፡፡ የትራምፕ አስተዳደር “የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተቻለውን ጥረት እያደረገ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“እኛ ማድረግ ያለብን ሰዎች በዚህ እንዳይሞቱ የሚያስችሉ የተለያዩ የህክምና አማራጮች እንዲኖሩ ማድረግ ነው” ማለታቸውም ነው የተገለጸው፡፡
በአሜሪካ ቅዳሜ ዕለት ብቻ 84,000 የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን እስከ እሁድ ድረስ በሀገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 8,575,000 መድረሱን ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ገልጿል፡፡
የቫይረሱ ጉዳይ የትራምፕና የባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ዋነኛ አጀንዳ መሆኑ ይታወቃል፡፡