እሽግ የፕላስቲክ ጠርሙስ ውሃ ከቧንቧ ውሃ 3 ሺ 500 እጥፍ የሚልቅ ከባቢያዊ ተጽዕኖ እንዳለው አንድ ጥናት አመለከተ
ጥናቱ ተጽዕኖውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የፖሊሲ አማራጮች ሊኖሩ እንደሚገባ አመላካች ነውም ነው ተመራማሪዎቹ ያሉት
ጥናቱ እሽግ የፕላስቲክ ጠርሙስ ውሃ 1 ሺ 400 ጊዜ ያህል ስነ ምህዳርን የመጉዳት አሉታዊ አቅም እንዳለውም አመልክቷል
እሽግ የፕላስቲክ ጠርሙስ ውሃ ከቧንቧ ውሃ 3 ሺ 500 እጥፍ ተፈጥሯዊ አካባቢን የመበከል አቅም እንዳለው ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡
በዐይነቱ የመጀመሪያ ነው የተባለ ጥናት ሃይላንድ ውሃ በሚዘወተርበት ስፔን ባርሴሎና ‘ኢንስቲትዩት ፎር ግሎባል ሄልዝ’ በተባለ የምርምር ተቋም ተካሂዷል፡፡
በባርሴሎና ምንም አንኳን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የቧንቧ ውሃ አቅርቦትና ጥራቱ ቢሻሻልም እሽግ የሃይላንድ ውሃ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ግን ጨምሯል፡፡
ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ጥናቱ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ሃይላንድ ውሃ ቢጠጡ በሚል እሳቤ የተካሄደው፡፡
በዚህም የከተማዋን ነዋሪ የሃይላንድ ውሃ ፍላጎት ለማሟላት በዓመት የቧንቧ ውሃ ምርትን ለማቅረብ ከሚያስፈልገው በላይ በ3,500 እጥፍ የሚልቅ ወጪ እንደሚሻ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡
ተመራማሪዎቹ የፕላስቲክ ጠርሙስ ውሃ ከቧንቧ ውሃ በባሰ በ1 ሺ 400 እጥፍ ስነ ምህዳርን እንደሚጎዳም በጥናታቸው አረጋግጠዋል፡፡
ከቧንቧ ውሃ ጥራት ጋር የተያያዙ መጠነኛ የጤና እክሎች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም እክሎቹም ሆኑ ከእሽግ የፕላስቲክ ጠርሙስ ውሃ የሚገኘው ጥቅም ከሚደርሰው ከፍተኛ ከባቢያዊ ጉዳት ጋር ሊነጻጸሩ የሚችሉ እንዳልሆኑ ነው ዘ ጋርዲያን በዘገባው ዋቢ ያደረጋቸው ተመራማሪዎቹ የገለጹት፡፡
ከተመራማሪዎቹ አንዷ የሆኑት ክርስቲና ቪላኑኤቫ ጥናቱ የእሽግ ውሃ ፍጆታን ለመቀነስ ቢያግዝም ተጽዕኖውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የፖሊሲ አማራጮች ሊኖሩ እንደሚገባ አመላካች ነው ብለዋል፡፡