ቤተክርስቲያኗ ጠ/ሚንስትር አብይና አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ይካሄዳል የተባለውን የኤጲስ ቆጰሳት ሹመት እንዲያስቆሙ ጠየቀች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በትግራይ ይደረጋል የተባለው የኤጲስ ቆጰሳት ሹመትን አወገዘች
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተገንጥያለው ያለው የትግራይ ሲኖዶስ የፊታችን እሁድ የኤጲስ ቆጰሳት ሹመት እሰጣለሁ ማለቱ ይታወሳል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በትግራይ ይደረጋል የተባለው የኤጲስ ቆጰሳት ሹመትን አወገዘች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ባወጣችው መግለጫ በትግራይ ክልል ሐምሌ 9 ይደረጋል የተባለው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሕገ ቤተ ክርስቲያንና አንቀጽ 37 እና 38 ያላከበረ ነው ብላለች።
ቤተ ክርስቲያኗ አክላም ይሰጣል የተባለው ሹመት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር ተገቢ ያልሆነ የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት የሚጥስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚጎዳና በጦርነት የተጎዳውን ሀብት ንብረቱ የወደመበትን ገዳማቱና አብያተ ክርስቲያናቱ የተጎዱበትን ሕዝብ የማይጠቅም ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል ብላለች።
- ልኡኩ በትግራይ ክልል ካሉ አባቶች ጋር ሊያደርግ የነበረው ውይይት አልተሳከም አለ
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትግራይ ህዝብን ይቅርታ ጠየቀች
ሲኖዶሱ በመግለጫው በክልል ትግራይ በተካሄደው ጦርነት በቤተ ክርስቲያናችን የበላይ መዋቅርና በክልል ትግራይ አህጉረ ስብከት መካከል የነበረው አስተዳደራዊ መዋቅር ተቋርጦ መቆየቱን ተከትሎ የተፈጠረው አለመግባባት በውይይት ተፈቶ መዋቅራዊ አንድነታችን በድጋሚ ተጠናክሮ እንዲቀጠል ሀገራዊ የሰላም እርቁ ከተፈጸመበት ማግስት ጀምሮ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፊርማ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ሲጠየቅ መቆየቱን አስታውቃል።
ምንም እንኳን ቅዱስ ሲኖዶሱ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም በክልሉ ያሉት ብፁዓን አባቶችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተከፈተው የሰላምና የውይይት በር ከመጠቀም ይልቅ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በመጣስ መንበረ ሰላም የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት መሥርተናል በሚል ተገቢነት የሌለው መግለጫ ከመስጠትም አልፎ ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት መፈጸም አለበት የሚል ውሳኔ በማሳለፍ 10 ኤጲስ ቆጶሳትን ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዐ.ም. ለመሾም ፕሮግራም መያዙን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ መስጠታቸውንም አስታውቋል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ በጦርነቱ ወቅት ለነበረው የመዋቅራዊ ግንኙነት ጉድለትና የሰብአዊ ድጋፍ እጥረት በይፋዊ መግለጫ ይቅርታ የተጠየቀ ቢሆንም ለይቅርታው አዎንታዊ ምላሽ አለመሰጠቱ በእጅጉ እንዳሳዘናትም ቤተ ክርስቲያኗ ገልጻለች።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለችግሩ መፈታት ባላት ቁርጠኝነት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ የሰላም ልዑክ ወደ ክልሉ በመላክ በክልሉ ለደረሰው ጉዳት ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል ሃያ ሚሊየን ብር ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያስረከበች ሲሆን በዚህም ወቅት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለተደረገው አቀባበል ቅዱስ ሲኖዶስ አመስግኗል፡፡
ይሁን እንጁ የሰላም ልዑኩ ዋና ተልእኮ የሆነውን በክልሉ ከሚገኙ ብፁዓን አባቶች ጋር ለመወያየት የተያዘውን አጀንዳ በተመለከተ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የተመራው የሰላም ልዑክ በመቀሌ ሀገረ ስብከት በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል የተገኘ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን በመዘጋቱ ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ በእጅጉ እንዳሳዘነውም የሲኖዶሱ መግለጫ ያስረዳል፡፡
በመሆኑም የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም በትግራይ ክልል ሐምሌ 9 ይደረጋል የተባለው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እና ሹመት ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑ ተገልጿል።
በትግራይ ክልል ተከስቶ የነበረውን ችግር የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ችግሩን በውይይት የፈቱት መሆኑ እየታወቀ የሰላም ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን እስካሁን ሰላም መፈለጓ ያልተቋረጠ ቢሆንም አለመሳካቱ የሚያሳዝን በመሆኑ ለሰላም የሚደረገው ጥረት ዘላቂ መፍትሔ እስከሚገኝ ድረስ የማይቋረጥ መሆኑንም ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እየተደረገ ያለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ያልተከተለ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እንዲያስቆሙል ስትል ቤተ ክርስቲያኗ ጠይቃለች።
እንዲሁም ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ችግሮቹ በውይይት እንዲፈቱ መንግሥታዊ እገዛ በማድረግ የውይይት መድረክ እንዲያመቻቹም ቤተ ክርስቲያኗ ጥሪ አቅርባለች።
በመላው ዓለም የሚገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ሕዝበ ክርስቲያን እናት ቤተ ክርስቲያናችሁ ያስተላለፈችውን የሰላም ጥሪ ተግባራዊ ሆኖ አንድነቷ ጸንቶ ይኖር ዘንድ በጸሎት ተግጋችሁ ከቤተ ክርስቲያናችሁ ጎን እንድትቆሙ ስትልም ጠይቃለች።