የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከመንግስት ጋር እየተነጋገረች መሆኑን አስታወቀች
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እና ፖትሪያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስና ልዑካቸው እየመከሩ መሆኑን ቤተ-ክርስቲያን አስታወቀች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያ ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጧ አይዘነጋም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያ ፓትሪያርክና ሊቃነ ጳጳሳትን ያካተተ ልዑክ በቤተ-መንግሥት ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋር እየመከረ መሆኑን ቤተክርስቲያኗ አስታውቃለች
ቤተ-ክርስቲያኒቷ ደረሰብኝ ላለችው መንግታዊ ጫናና ለገጠማት ችግር ምላሽ እንዲሰጣት እየጠየቀች ነው።
ህገወጥ በተባለው የጥር 14ቱ ኤጲስ ቆጶሳት ሲመት ምክንያት ውጥረት ውስጥ ያለችው ቤተክርስቲያኗ፤ መንግስትን በጣልቃ ገብነትና ህገ-ወጥ ላለችው ቡድን ድጋፍ በመስጠት ተችታለች።
ቤተክርስቲያኗ መንግስት ልእልናዋን የማያስጠብቅ ከሆነ የካቲት አምስት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሰልፍ ጠርታለች።
ምንም እንኳ ይህን ሰልፍ መንግስት "ህገ-ወጥና ለሌላ ዓላማ ሊውል ይችላል" በሚል ከለከልኩ ቢልም፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ውሳኔ አልቀበልም ብሏል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የቤተ- ክርስቲያኒቱን ጥሪ መሰረት በማድረግ በሽማግሌዎች በኩል እንወያይ ማለታቸውን ቤተክርስቲያኗ ገልጻለች።
ለምዕመናን ደህንነትና ስጋት ሲባል የመንግስትና የቤተ-ክርስቲያንን ተቃርኖ ፈር ያስይዛል ተብሎ የሚጠበቀው "ውይይት" በቤተ-መንግስት እየተካሄደ ነው ተብሏል።
የቤተ-ክርስቲያኗ ፓትሪያርክና ሊቃነ ጳጳሳትን ያካተተ ልዑክ በቤተ-መንግስት እየመከረ እንደሆነ ጠቅላይ ቤተ-ክነት የህዝብ ግንኙነት በመግለጫው አስታውቋል።
ምዕመኑ አባቶች የደረሱበትን ውጤት እስኪያሳውቁ ድረስ በትእግስት እንዲጠብቅ አሳስቧል።
ቤተክርስቲያኗ ከቀኖና እና ከስርአተ ቤተክርስቲያን ውጭ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ከቤተክርስቲያን እንዲለዩ እና እንዲወገዙ ያደረገቻቸውን "ቡድኖች" መንግስት እየደገፈ ነው የሚል ክስ ቤተክርስቲያኗ አቅርባለች።
መንግስት ጣልቃ እንዳልገባና ችግሩም በቤተክርስቲያኗ አሰራር እንደሚፈታ ቢገልጽም ቤተክርስቲያኗ ግን መንግስት "ህገወጦችን" በማገዝ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት እንዲሰበሩ፣ መንበረ ጵጵስናዎች እንዲያዙ፣ ምእመናን እንዲዋከቡ እና እንዲገደሉ አድርጓል የሚል ክስ አቅርባለች።