ቤተክርስቲያኗ ካወገዘቻቸው "ቡድኖች" ጋር እኩል መታየቷን ተቃወመች
ሲኖዶሱ ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤተክርስቲያኗ የተፈጠረውን ችግር ቀላል ነው ማለታቸውን ተቃውሟል
ሲኖዶሱ በቤተክርስቲያኗ የሀይማኖት አባቶች ላይ ወከባ እየደረሰ ነው ብሏል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በቀኖና ጥሰት ካወገዘቻቸው "ህገወጥ ቡድኖች" ጋር በአቻ መታየቷ ትክክል አይደለም ስትል ተቃውሞዋን ገለጸች።
የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከትናንት በስትያ ከካቢኔያቸው ጋር ባደረጉት ስብሰባ መንግስታቸው የሚደግፈውም ሆነ የሚቃወመዉ ኃይለ የለም ማለታቸውን ተቃውሞ መግለጫ አውጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "በተለየ የምንደግፈው፤ በተለየ የምንቃወመው ኃይል የለም፡፡ ሁሉም ሃይሎች ኦርቶዶክሶች ናቸው፤ ሁለቱም ጋር ያሉ ጥያቄዎች እውነትነት አላቸው“ ነበር ያሉት።
ሲኖዶሱ ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤተክርስቲያኗ የተፈጠረውን ችግር ቀላል ነው ማለታቸውንም ተቃውሟል።
"ጠቅላይ ሚኒስትሩ ...ጉዳዩ ቀላል እና በንግግር የሚፈታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ አገላለጽ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት እና ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፋቸውን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ውሳኔዎች ያላቸውን ውጤት ወደ ጎን የተወ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታምናለች፡፡ "ብሏል ሲኖደሱ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተክርስቲያኗ ህገወጥ ናቸው ካለቻቸው አካላት ጋር በአቻ በማየት ሊወያዩ ይገባል ማለታቸው "ህገወጥነትን የሚያበረታታ" ነው ስትል ተቃውማለች።
የካቢኔ አባላት እጃቸውን እንዳያስገቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው መመሪያም የሲኖዶሱን ውሳኔ እና የቤተክርስቲያንን ህጋዊ ሰውነት አክበረው የህዝብን ሰላም ደህንነት ለመጠበቅ ጥረት የሚያደርጉ አስፈጻሚ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ ያደርጋል ብሏል ሲኖደሱ።
በቤተክርስቲያኗ የሀይማኖት አባቶች ላይ ወከባ እየደረሰ መሆኑን የገለጸው ሲኖዶሱ ህገወጥ የተባሉት ቡድኖች ግን በተለያዩ ቦታዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሊታረም የሚገባው ነው ያለው ሲኖዶሱ "መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን የሕግ የበላይነትና የተቋማትን ደህንነት የማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ" ጠይቋል።
ባለፈው ሳምንት በደቡብ ምእራብ ሽዋ ሀገር ስብከት ሶስት የሀይማኖት አባቶች ለሌሎች 26 ኢጲስ ቆጶሳት ሹመት ሰጥተናል ማለታቸውን ተከትሎ ነበር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተ ተዋህዶ ቤተክርስቲያ ከባድ የተባለ ችግር የተፈጠረው፡፡
በዚህ ምክንያት ቤተክርስቲያኗ አስቸኳይ የሲኖዶስ ጉባኤ በመጥራት፤ ከቤተክርስቲያኗ ቀኖና ስርአት ውጭ የኢጲስ ቆጶሳት ሹመት ያደረጉት ሶስት የኃይማኖት አባቶች እንዲወገዙ እና ከቤተክርስቲያን እንዲለዩ መወሰኗ ይታወሳል፡፡
ተወግዘው ከቤተክርስቲያን እንዲለዩ የተደረጉት አባ ሳዊሮስ እና ሹመት የተቀበሉት ሁሉም ከድቁና ጀምሮ ያለው ስልጣነ ክህነታቸው እንዲነሳም ጉባኤው ወስኗል፡፡
በሲኖዶሱ የተወገዙት አባቶች ከቋንቋ እና ሀብት ክፍፍል ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለ እየገለጹ ሲሆን የሲኖዶሱን ውሳኔም እንደማይቀበሉት እየተናሩ ናቸው፡፡
ሲኖዶሱ በቀኖና ጥስት የተወገዙት ሶስት አባቶች ጨምሮ ሌሎችም በኦሮምኛ ቋንቋ ሀይማኖታዊ ትምህርት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጿል፤ በቋንቋ እንዳንጠቀም ተጽእኖ አድሮብናል የሚባለው ትክክል አይደለም ብሏል።
ሲኖዶሱ የቀኖና ጥሰት ፈጸመዋል የተባሉት አባቶች ይቅርታ የሚጠይቁ ከሆነ ቤተክርስቲያኗ እንደምትቀበላቸው መግለጹ ይታወሳል፡፡