ታይዋን የባህር እና የአየር ሃይሏን በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን አዘዘች
ከ20 በላይ የቻይና አውሮፕላኖች በታይዋን የአየር ክልል አቅራቢያ መታየታቸውን ተከትሎ ነው ታይፒ ዝግጁነቷን ያጠናከረችው
የራስ ገዝ ደሴቷ ጉዳይ ቤጂንግ እና ምዕራባውያንን ማፈጠጡን ቀጥሏል
ታይዋን የጦር አውሮፕላኖች እና ሚሳይሎቿ ለአስቸኳይ እርምጃ ዝግጁ እንዲሆኑ ማዘዟ ተነግሯል።
የቤጂንግ ተዋጊ አውሮፕላኖች እና የጦር መርከቦች እንቅስቃሴ አሳሳቢ ነው በሚል ነው ታይፒ ትዕዛዙን ያስተላለፈችው።
በትናንትናው እለትም 20 የቻይና አውሮፕላኖች ታይዋን እና ቻይና ከ1949 ጀምሮ እንደ የጋራ የአየር ቀጠና የሚቆጥሩትን የአየር ክልል ማቋረጣቸውን የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የቤጂንግ የጦር አውሮፕላኖች በታይዋን ሰርጥ የማንዣበባቸው ጉዳይ አዲስ ባይሆንም እየተጠናከረ መሄዱ ግን ታይፒን እንዳሳሰባት ተገልጿል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግም ዛሬ በጃፓን ጉብኝት ሲያደርጉ፥ ቻይና ከሩሲያ ጋር በመሆን የእስያን ብሎም የአውሮፓን ሰላም ለማወክ እየሰራች ነው በሚል ወቅሰዋል።
“ጎረቤቶቿን የመረበሽና ታይዋንን አደጋ ላይ የመጣል” እንቅስቃሴዋን እንድታቆምም ነው ዋና ጸሃፊው ያሳሰቡት።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ኔቶ በማይመለከተው ጉዳይ እጁን ማስገባቱን እንዲያቆም ማሳሰቡን አሶሼትድ ፕረስ አስነብቧል።
ሚኒስትሩ ማኦ ኒንግ “የእስያ ፓስፊክ ቀጠና የሀገራት የጂኦፖለቲካ የበላይነት ማስጠበቂያ የትግል ሜዳ አይሆንም፤ የቀዝቃዛው ጦርነት አይነት ጎራ ለይቶ ማራኮቻ እንዲሆንም አንፈቅድም” ነው ያሉት።
አሜሪካ ለታይዋን የጦር መሳሪያ ለመሸጥ መስማማቷ እና የቀድሞ የኮንግረንሱ አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ታይፒን የመጎብኘታቸው ጉዳይ ቤጂንግን ክፉኛ ማስቆጣቱ ይታወሳል።
ዋሽንግተንም የራስ ገዝ ደሴቷን ከቤጂንግ ጥቃት ለመመከት ቃል መግባቷ በኢኮኖሚ የፈረጠሙትን ሀገራት ማፋጠጡም አይዘነጋም።
የፊታችን እሁድ ቤጂንግ የሚገቡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም፥ የሻከረውን ግንኙነት ማደስ የሚያስችሉ ምክክሮችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ቤጂንግ የሉአላዊ ግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥራት ራስ ገዟ ታይፒ፥ እንደ ዩክሬን ሁሉ የሃያላኑ መፋለሚያ ልትሆን እንደምትችል ግን ተንታኞች ያነሳሉ።
የአሜሪካ አየር ሃይል ባለአራት ኮከብ ጀነራሉ ማይክ ሚንሃንም አሜሪካ እና ቻይና በ2025 ወደ ጦርነት ሊገቡ እንደሚችሉ ስጋታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
ፔንታጎን ይህ መረጃ ከወታደራዊ ግምገማዬ ጋር አብሮ አይሄድም ቢልም፥ በታይዋን ሰርጥ የሚታየው እንቅስቃሴ ውጥረቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው።