“ጥምቀት በውኃ ላይ” በደምበል (ዝዋይ) ኃይቅ ላይ የተከበረው የከተራና ጥምቀት በዓል
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የደምበል (ዝዋይ) ኃይቅ የጥምቀት በዓልን ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል
የጥምቀት በዓል ከተከበረባቸው ቦታዎች መካከል በደምበል (ዝዋይ) ሐይቅ ውስጥ የሚገኙት ገዳማት ይጠቀሳሉ
የደምበል (ዝዋይ) ኃይቅ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሽዋ ዞን ከባቱ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ለቱሪስት መስህበነት ተመራጭ ከሆኑ ስፍራዎችና በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የስምጥ ሸለቆ ኃይቆች አንዱ ነው።
ደምበል ኃይቅ በውስጡ ገሊላ፣ ደብረሲና፣ ደብረፂዮን፣ ጠደቻና ፉንድሮ የተሰኙ ደሴቶች ያሉት ሲሆን፤ በደሴቶቹ ላይ የአቡነ ተክለሃይማኖት፣ ቅዱስ ሚካኤል፣ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም፣ አርባዕቱ እንስሳትና ፀዴቻ አቡነ አብርሃም ገዳማት ይገኛሉ።
ከአምስቱ ገዳማት አቡነ ተክለሃይማኖትና ደብረ ጽዮን ከደሴታቸው በመውጣት ሦስት ኪሎ ሜትር የሚሆነውን የሐይቁን ክፍል አቋርጠው ምድር ላይ በማክበር ብቸኛ ያደርጋቸዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው የዘንድሮው የከተራ በዓል በሌሎች የሀገሪቱ አከባቢዎች እንደተከበረ ሁሉ በባቱ ደምበል (ዝዋይ) ኃይቅም በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉን በተመለከተ ከአል-ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ የጥምቀትን በዓል በደምበል ኃይቅ ማክበር የተጀመረው ከጥንት ጀምሮ መሆኑን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ኃይቁ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ባለመነገሩ በሚፈለገው ደረጃ ሳይተዋወቅ መቆየቱን አስታውቀዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚመጡ ሰዎች በተገኙበት የአከባቢው ማህበረሰብ የጥምቀት በዓልን በደምበል ኃይቅ በድምቀት ሲያከበር ቆይታል ያሉት ምክትል ኮሚሽሩ፤ በቀጣይ የበዓሉን ተሳታፊወችንም ሆነ የጎብኚዎች ቁጥር
ለመጨመር በክልሉ የቱሪዝም ኮሚሽን አማካኝነት በርካታ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እዚህ ከተማ መጥተው የጥምቀት በዓልን እንዲያከብሩ እየሰራን ነው” ሲሉም አስታውቀውዋል።
በአከባቢው ለቱሪዝም መስህብነት የሚያገለግሉ እንደ አቢያታ ሻላ ብሄራዊ ፓርክ እና ወፎች ብቻ የሚታዩበት የወፎች ፓርክ መኖራቸውን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ይህም አካባቢውን በዓሉን ለሚያከብሩ ሰዎች ተመራጭ ያደርገዋል ብለዋል።
ኮሚሽኑ የአከባቢው ማህበረሰብ በተለይም ወጣቶች በማህበር በመደራጀት በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ተጠቃሚ ሚሆኑበት ስራ ለመስራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እንደ አዲስ ከተዋቀረ አንድ ዓመት ከግማሽ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ነጋ፤ “በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ግማሽ ሚልየን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድሎች ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ ነው” ብለዋል።