ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ ካደርጓቸው 51 ግጥሚያዎች ሊቨርፑል 21ዱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የሊጉን ፉክክር ይበልጥ አጓጊ የሚያደርጉ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ማንቸስተር ሲቲ በኢትሃድ ሊቨርፑልን የሚያስተናግድበት ጨዋታ 8 ስአት ከ30 ይጀምራል።
ሲቲ አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው ከአርሰናል በ8 ነጥብ ዝቅ ብሎ በ61 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ሊቨርፑል በበኩሉ በኒውካስትል በአምስት ነጥብ ተበልጦ በ42 ነጥብ 6ኛ ላይ ይገኛል።
በስምንት ቀናት ውስጥ ከሊጉ ዋና ዋና ቡድኖች ጋር የሚጫወቱት ቀያዮቹ በቀጣይ ከቼልሲና ከአርሰናል ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም የየርገን ክሎፕን ቡድን እስከ 4ኛ ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ወሳኝ ናቸው።
የቀድሞው የሊቨርፑል ተጫዋች ዳኒ መርፊም ቀያዮቹ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ ቢያንስ ሁለቱን ፍልሚያዎች ማሸነፍ እንዳለባቸው ተናግሯል።
ከ2017 እስከ 2022 ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል አራት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ ሁለት የኤፍ ኤ ካፕ፣ አንድ የሻምፒዮንስ ሊግ፣ የአውሮፓ ሊግ እና የክለብ የአለም ዋንጫዎች አንስተዋል።
ከሁለት አንዱ ባለፉት አምስት አመታት ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜም ደርሰዋል፤ የፕሪሚየር ሊጉ የአመቱ ኮከብ ተጫዋችም ባለፉት አምስት አመታት ወይ ከኢትሃድ ነው አልያም ከአንፊልድ ነው የተመረጠው።
የፔፕ ጋርዲዮላ እና የርገን ክሎፕ ትንቅንቅ ከቀድሞዎቹ የማንቸስተር ዩናይትድ እና አርሰናል አሰልጣኞች አሌክስ ፈርጉሰን እና አርሰን ቬንገር በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ድምቀት መሆኑንም ብዙዎች ይመሰክራሉ።
የሁለቱን ክለቦች የውድድር ታሪክ ስንመለከት ግን ሊቨርፑል በማንቸስተር ሲቲ ላይ የበላይነት አለው።
በፕሪሚየር ሊጉ 51 ጊዜ ተገናኝተው ቀያዮቹ በ21ዱ ሲያሸንፉ ውሃ ሰማያዊ ለባሾቹኡ በ19ኙ ረተዋል፤ በአጠቃላይ እስካሁን ካደረጓቸው 151 ጨዋታዎች ሊቨርፑል በ91ዱ በማሸነፍ ድንቅ ታሪክ አጽፏል(ሲቲ 50 ጨዋታዎችን አሸንፏል)።
ካለፉት አራት ጨዋታዎችም (ኤፍ ኤ ካፕ እና ኮሚዩኒቲ ሺልድን ጨምሮ) ሶስቱን ያሸነፉት ቀያዮቹ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በአንፊልድ ካደረጓቸው 17 ጨዋታዎች በዘጠኙ ተሸንፎ በአንዱ ብቻ ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ ዛሬ በኢትሃድ የምንጊዜም ተቀናቃኙን ይገጥማል።