ዩዜን ቦልት ከማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ጋር ተገናኘ
የስምንት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ቴን ሀግ “የዩናይትድን ክብር ዳግም ስለመለሱ አመስግኛቸዋለሁ” ብሏል
ጃማይካዊው የአጭር ርቀት ንጉስ ከአሰልጣኙ ጋር ስለተጫዋቾች ዝውውርም መወያየታቸውን ተናግሯል
የአለማችን ፈጣኑ የአጭር ርቀት ሯጭ ዩዜን ቦልት ከማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ጋር በኦልትራፎርድ ተገናኝቷል።
ጃማይካዊው የዩናይትድ ቀንደኛ ደጋፊ ቀያዮቹ ሰይጣኖች በኤፍ ኤ ካፕ ፉልሃምን ከመመራት ተነስተው 3 ለ 1 ያሸነፉበትን ጨዋታ ተመልክቷል።
ከጨዋታው በኋላም ከኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ጋር ተገናኝቶ ለአጭር ደቂቃም ቢሆን ስለክለቡ መነጋገራቸውን ነው ቦልት የገለጸው።
ዩናይትድ በኤሪክ ቴን ሀግ ዘመን የካራባኦ ዋንጫን በማንሳት የድል ጉዞውን ጀምሯል የሚለው ቦልት፥ የኤፍ ኤ ካፕ እና የአውሮፓ ሊግ ጉዞውም የሚደነቅ መሆኑን ለኢንዲፔንደንት ተናግሯል።
ቀያዮቹ ሰይጣኖች በኤፍ ኤ ካፕ ግማሽ ፍጻሜ ከብራይተን ጋር በዌንብሌይ የሚጫወቱ ሲሆን፥ በአውሮፓ ሊግም በሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ ከስፔኑ ሲቪያ ጋር ይፋለማሉ።
ክለቡ ከ2017 በኋላ ዳግም ወደ ዋንጫ ፉክክር መመለሱ እንዳስደሰተው የተናገረው ጃማይካዊው የአጭር ርቀት ንጉስ፥ “ቴን ሃግን እንደጨበጥኩት አመሰግናለሁ አልኩት፤ ለምኑ? የሚል ጥያቄ ሲያስከትልም የክለቡን የክብር ዳግም ስለመለስክ” አልኩት ይላል።
“አሁን ዩናይትድን መመልከት ያስደስታል፤ የክለቡ አንድነት ተመልሷል፤ የጋራ ጥረታቸውና ቆራጥነታቸው በውጤት እያታየ ነው፤ (ቴን ሃግ) ቡድኑን ያሻሻለበትን መንገድ አደንቃለሁ” ሲልም ተደምጧል።
በቀጣዩ የክረምት የዝውውር መስኮት ስለሚደረጉ የተጫዋቾች ዝውውር አሰልጣኙን ጠይቄው “አንተ ምን ታስባለህ?” የሚል ጥያቄ አንስቶልኛል ያለው ቦልት፥ ቀላልና ደስ የሚል ቆይታ ስለማድረጋቸው ተናግሯል።
የስምንት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ዩዜን ቦልት የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋቾች ጠንክረው የሚሰሩትና ለድል የሚዋደቁት ኔዘርላንዳዊውን አሰልጣኝ ለማስደሰት እንደሆነ ያምናል።
ይህም በቀደሙት አሰልጣኞች ያልታየ መነቃቃትን ፈጥሮ ቴን ሃግ በዋንጫ የታጀበ የድል ጉዞ እያደረጉ መሆኑንም በእንግሊዝ በሰጠው ቃለምልልስ ተናግሯል።