ኢርዶጋን አሜሪካ እና ዩኬ ቀይ ባህርን ወደ "ደም ባህር" ለመቀየር እየሞከሩ ነው ሲሉ ከሰሱ
ኢርዶጋን፣ አሜሪካ እና ዩኬ በየመን ያደረጉት ድብደባ ተመጣጣኝ አይደለም ነው ብለዋል
የቀይ ባህርን የመርከብ እንቅስቃሴ ሰላማዊ አደርጋለሁ የምትለው አሜሪካ ሌሎች ሀገራትን በማስተባበር በሀውቲዎች ላይ ጥቃት ከፍታለች
ኢርዶጋን አሜሪካ እና ዩኬ ቀይ ባህርን ወደ "ደም ባህር" ለመቀየር እየሞከሩ ነው ሲሉ ከሰሱ።
የቱርኩ ፕሬዝደንት ጣይብ ኢርዶጋን አሜሪካ እና ዩኬ ቀይ ባህርን ወደ "ደም ባህር" ለመቀየር እየሞከሩ ነው ሲሉ ከሰዋል።
ኢርዶጋን፣ አሜሪካ እና ዩኬ በየመን ያደረጉት ድብደባ ተመጣጣኝ አይደለም ነው ብለዋል።
በምዕራባውያን የሚዘወረው ኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ፣ የፍልስጤሙን ታጣቂ ቡድን ለማጥፋት በጋዛ ጦርነት እያካሄደች ያለችውን እስራኤልን አጥብቃ አውግዛለች፣ የእስራኤልን ዘመቻ ደግፈዋል ያለቻቸውን ምዕራባውያንንም ተችታለች።
አሜሪካ እና ዩኬ የየመኑ ሀውቲ አማጺ በቀይ ባህር የመርከብ እንቅስቃሴ ላይ ላደረሰው ጥቃት ለመበቀል በየመን ስላደረሱት ድብደባ የተጠየቁት ኢርዶጋን ጥቃቱ ተመጣጣኝ አይደለም ብለዋል።
ኢርዶጋን "የደረሰው ጥቃት ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ኢርዶጋን "በአሁኑ ወቅት ቀይ ባህር የደም ባህር ለማድረግ እየሞከሩ ነው፣ የመን ከሀውቲዎች ጋር በመሆን ሁሉንም ኃይሏን በመጠቀም፣ ለአሜሪካ እና ለዩኬ አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት አለባት" ብለዋል።
አለም አቀፍ እውቅና ያለውን የየመን መንግስት የምትደግፈው ቱርክ፣ በእሱ እና አብዛኛውን የየመን ክፍል በተቆጣጠሩት የሀውቲ ታጣቂዎች መካከል እርቅ የመፍጠር አላማ ያለውን በተመድ የሚመራውን ሂደትም ትደግፋለች።
ኢርዶጋን የሀውቲ ታጣቂዎች ከአሜሪካ እና ከዩኬ የተቃጣባቸውን ጥቃት ስኬታማ በሆነ መንገድ መከላከላቸውን ከበርካታ ምንጮች መስማታቸውን እና ኢራንም ሊቃጡባት ከሚችሉ ጥቃቶች ለመከላከል መዘጋጀቷን ተናግረዋል።
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር የሚንቀሳቁሱ መርከቦችን የሚያጠቁት ለፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ድጋፍ ለማሳየት መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል።
የቀይ ባህርን የመርከብ እንቅስቃሴ ሰላማዊ አደርጋለሁ የምትለው አሜሪካ ሌሎች ሀገራትን በማስተባበር በሀውቲዎች ላይ ጥቃት ከፍታለች።