ፕሬዝደንት ኢርዶጋን ከሀማስ መሪ ጋር በቱርክ ተወያዩ
በፕሬዝደንቱ እና በሃኒየህ የሚመራ የልኡካን ቡድን መካከል የተካሄደው ይህ ውይይት እስራኤል ጋዛን ማጥቃት ከጀመረች ወዲህ የመጀመሪያ ነው
ፕሬዝደንት ኢርዶጋን በቀጠናው ፍትሀዊ እና ዘላቂ ስላም ለመፍጠር በሚደረጉ ጥረቶች ጉዳይ ከሀማስ መሪ በኢስታንቡል መምከራቸውን የፕሬዝደንቱ ጽ/ቤት አስታውቋል
ፕሬዝደንት ኢርዶጋን ከሀማስ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ጋር በቱርክ ተወያይተዋል።
የቱርኩ ፕሬዝደንት ኢርዶጋን የሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ ለማስገባት እና በቀጠናው ፍትሀዊ እና ዘላቂ ስላም ለመፍጠር በሚደረጉ ጥረቶች ጉዳይ ከሀማስ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ጋር በትናትናው እለት በኢስታንቡል መምከራቸውን የፕሬዝደንቱ ጽ/ቤት አስታውቋል።
በፕሬዝደንቱ እና በሃኒየህ የሚመራ የልኡካን ቡድን መካከል የተካሄደው ይህ ውይይት እስራኤል ጋዛን ማጥቃት ከጀመረች ወዲህ የመጀመሪያ ነው።
ሀኒየህ ወደ ቱርክ ያቀናው ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊዲን ጋር ባለፈው አርብ በኳታር ዶሃ ከተገናኘ ከሶስት ቀናት በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
"እስራኤል በፍልስጤም መሬት በተለይም በጋዛ እያደረሰች ያለው ጥቃት፣ እርዳታ ያለማቋረጥ እንዲገባ የሚደረጉ ጥረቶች እና በቀጠናው ፍትሀዊ እና ዘላቂ ሰላም የማስፈን ጉዳይ ውይይት ተደርጎባቸዋል" ሲል የቱርክ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ጉብኝቱ የተካሄደው እስራኤል በኢራን ላይ አድርሳዋለች በተባለው ጥቃት ምክንያት ቀጣናዊ ውጥረት በተፈጠረበት ወቅት ነው።
መግለጫው እንዳለው "ኢርዶጋን በቀጠናው ከተፈጠረው ውጥርት (እስራኤል እና በኢራን መካከል) መጠቀም እንደሌላባት እና የጋዛ ጉዳይ በድጋሚ ትኩረት ማግኘት እንዳለበት እስምረው ተናግረዋል።"
የምዕራባውያን ወታደራዊ ጥምረት ኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ፣ እስራኤል የጥቅምት ሰባቱን የሀማስ ጥቃት ተከትሎ በጋዛ እያካሄደች ያለውን ጥቃት ማውገዟ ይታወሳል።
ያለቅድመ ሁኔታ እስራኤልን ይረዳሉ ያሏቸውን ምዕራባውያንን ያወገዙት ኢርዶጋን ሀማስን "የነጻነት ንቅናቄ" ሲሉ ጠርተውታል።
እንደመግለጫው ከሆነ ፕሬዝደንቱ በትናንትናው ስብሰባ ቱርክ ዘላቂ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ነጻ የፍልስጤም ሀገር እንዲመሰረት የዲፕሎማሲ ጥረቷን እንደምትቀጥልበት ለሀኒየህ ነግረውታል።
ኢርዶጋን ፍልስጤማውያን በአንድነት መቆም እንዳለባቸውም ለሀኒየህ ጨምረው መንገራቸውን መግለጫው ጠቅሷል።
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ከፍልስጤም አስተዳደር ጋር ያካሄደውን እና ለአጭር ጊዜ የቆየውን የእርስበእርስ ጦርነት ተከትሎ በ2007 የተካሄደውን ምርጫ በማሸነፍ ጋዛን ሲቆጣጠር፣ የፍልስጤም አስተዳደሩ ግዛት በዌስባንክ እንዲገደብ ሆኗል።
በስልጣን ክፍፍል ምክንያት የተጋጩትን ሁለቱን አካላት ለማሸማገል የተካሄዱ ጥረቶች እስካሁን አልተሳኩም።