ሀማስ የራሱን የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ ለአደራዳሪዎች አቀረበ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኔያሚን ኒታንያሁ ጽ/ቤት ሀማስ ለአደራዳሪዎቹ ያቀረበው የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ "እውነታ ላይ ያልተመሰረተ ነው" ሲሉ አጣጥለውታል
ሀማስ የእስራኤል ታጋቾችን እስከ እድሜ ልክ በተፈረደባቸው ፍልስጤማውያን እስረኞች የሚለቀቁበትን ዝርዝር ሁኔታ የሚያካትተውን የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ አቅርቧል
ሀማስ የራሱን የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ ለአደራዳሪዎች አቀረበ።
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ የእስራኤል ታጋቾችን እስከ እድሜ ልክ በተፈረደባቸው ፍልስጤማውያን እስረኞች የሚለቀቁበትን ዝርዝር ሁኔታ የሚያካትተውን የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ ለአደራዳሪዎቹ እና ለአሜሪካ ማቅረቡን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሃማስ ባቀረበው የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ እንደገለጸው ሴቶች፣ ህጻናት፣ በእድሜ የገፉ እና ህመምተኛ የሆኑ ታጋቾች ከ700-1000 በሚሆኑ ፍለስጤማውያን እስረኞች በመጀመሪያው ዙር እንዲለቀቁ ይደረጋል።
በምክረ ሀሳቡ መሰረት የታገተችው የእስራእል ሴት ወታደርም ትለቀቃለች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኔያሚን ኒታንያሁ ጽ/ቤት ሀማስ ለአደራዳሪዎቹ ያቀረበው የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ "እውነታ ላይ ያልተመሰረተ ነው" ሲሉ አጣጥለውታል።
ጽ/ቤቱ እንደገለጸው በዚህ ጉዳይ ያለው አዲስ ነገር ለጦር ካቤኔ እና ለሌሎች የጸጥታ አካላት ተሰጥቷል።
በጋዛ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት አደራዳሪዎቹ ግብጽ እና ኳታር፣ በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እየጣሩ መሆናቸውን ሮይተስ ዘግቧል።
ግብጽ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ፣ እርዳታ እንዲገባ እና በደቡብ እና ማዕከላዊ ያሉት ተፈናቃዮች ወደ ሰሜን ጋዛ እንዲመለሱ እንደምትፈልግ ፕሬዝደንት አቡዱል ፋታህ አልሲሲ በዛሬው እለት ተናግረዋል።
"እያወራን ያለነው በጋዛ ስለሚደረግ ተኩስ አቁም እና ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ ስለማድረስ ነው" ብለዋል ሲሲ።
ሲሲ እስራኤል በግብጽ ድንበር ባለችው የጋዛ ራፋ ላይ ለመክፈት ያቀደችውን ጥቃት አደገኛ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር የእስራኤልን ድንበር ጥሶ ያደረሰውን ከባድ የተባለ ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል እና በሀማስ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት እንደቀጠለ ነው፤ ሰላማዊ መፍትሄዎች እስካሁን አልተሳኩም።