እስራኤል ወታደሮቿ የትራምፕን የጋዛ እቅድ እንዳይተቹ አዘዘች
የመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ የእስራኤል ጦር መኮንኖችም ሆነ ወታደሮች ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማስወጣቱን እቅድ መቃወም አይችሉም ብለዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/08/273-124944-40e89340-e482-11ef-a819-277e390a7a08_700x400.jpg)
ሚኒስትሩ የእስራኤል ጦር ፍልስጤማውያን ከጋዛ የሚወጡበትን እቅድ እንዲያዘጋጅ ማዘዛቸው ይታወሳል
እስራኤል ጦሯ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይፋ ያደረጉትን ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማስወጣት እቅድ እንዳይተች አዘዘች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ አዲኡ ትዕዛዝ ተፈጻሚ እንዲሆን ለጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጀነራል ሀርዚ ሃቨሊ እና ለወታደራዊ ስለላ ክፍሉ መሪ ሜጀር ጄነራል ሽሎሚ ቤንደር መመሪያ መስጠታቸውንም ነው አል አይን አል አክባሪያ የዘገበው።
ካትዝ "የእስራኤል የጦር መኮንኖች በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወሳኝ እቅድ ዙሪያ አሉታዊ አስተያየት ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቅም" ያሉ ሲሆን ይህን መተላለፍ የሚያስከትለውን ቅጣት ግን አላብራሩም።
የእስራኤል ጦር አሁን ማተኮር ያለበት በፈቃዳቸው ከጋዛ መውጣት የሚፈልጉ ፍልስጤማውያንን ወደ ሌሎች ሀገራት እንዴት ይውጡ የሚለው እቅድ ላይ ብለዋል ሚኒስትሩ።
የወታደራዊ ስለላ ክፍሉ መሪ ሜጀር ጄነራል ሽሎሚ ቤንደር የትራምፕ ፍልስጤማውያንን አስወጥቶ ጋዛን የመቆጣጠር እቅድ የደህንነት ስጋት አለው የሚል አስተያየት መስጠታቸው ለካትዝ ማሳሰቢያ መነሻ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል።
የእስራኤሉ ቻናል 13 ቴሌቪዥን ከትናንት በስቲያ ሃሙስ በትራምፕ እቅድ ዙሪያ ዝቅ ወታደራዊ ምክክር መካሄዱን ዘግቧል።
ቤንደር በዚሁ ወቅትም የትራምፕ የጋዛ እቅድ በዌስትባክ ያለውን ውጥረት ሊያባብስ እንደሚችል መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
በቀጣዩ የረመዳን ወርም አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ጠቅሰው ስጋታቸው የትራምፕን የጋዛ እቅድ መቃወም እንዳልሆነ በትናንትናው እለት ለመከላከያ ሚኒስትሩ ማረጋገጣቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የቀድሞው የሪል ስቴት አልሚ ዳግም ወደ ስልጣን እንደተመለሱ ጋዛን "የመካከለኛው ምስራቅ ሬቬራ" አስመስለን ዳግም እንገነባታለን ብለዋል።
የፈራረሰችውን ጋዛ "የአለማችን ውብ መዳረሻ" ለማድረግ ግን ፍልስጤማውያን ከጋዛ መውጣት አለባቸው፤ እስራኤል ከጦርነቱ በኋላ ጋዛን ለአሜሪካ ታስረክባለች ማለታቸው ግን ፍልስጤማውያንን አስቆጥቷል።
በርካታ ሀገራትም የፕሬዝዳንቱ እቅድ ፍልስጤማውያንን ሀገር አልባ የሚያደርግ ነው በሚል ተቃውሟቸውን ቢገልጹም ትራምፕ በአቋማቸው ጸንተዋል።