“ነፍሳችንን ቢያስከፍለን እንኳን ጋዛን አንለቅም”- የጋዛ ነዋሪዎች
በትራምፕ ውሳኔ የተገረሙ የጋዛ ነዋሪዎች “ከጋዛ አንወጣም” ሲሉ ተቃውሞዋቸውን ገልጸዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/06/252-130204-whatsapp-image-2025-02-06-at-12.01.14-pm_700x400.jpeg)
ትራምፕ በዋይትኃውስ ከኔታንያሁ ጋር ሲመክሩ ጋዛን የመቆጣጠር እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋዛን የመቆጣጠር እቅድ እንዳላቸው መግለጻቸውን ተከትሎ በርካታ ፍልስጤማውያን ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።
በትራምፕ ውሳኔ የተገረሙ እና የተደናገጡ የጋዛ ነዋሪ ፍሊጤየማውያን “ጋዛን ለቀን አንወጣም” ሲሉ ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል።
በዴይር አል ባላህ በድንኳን መጠለያ ውስጥ የሚገኙ የጋዛ ነዋሪዎች ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የጋዛ ነዋሪዎችን በቋሚነት ወደ ሌላ ስፍራ ለማስፈር የተያዘው እቅድ እንዳስደነገጣቸው በመግለጽ እቅዱ ተቀባይነት የለውም ሲሉ እምቢተኝነታቸውን አመላክተዋል።
“ነፍሳችንን ቢያስከፍለን እንኳን ጋዛን አንለቅም” ያሉት ነዋሪዎቹ፤ “የትራምፕን ውሳኔ እንቃወማለን፣ ጦርቱን አስቁሟል፤ ነገር ግን እኛን ማፈናቀል ህይወታችን እንዲያበቃለት ያደርጋል” ብለዋል።
"በአሜሪካ የተሰራችው እስራኤል በጋዛ የሚገኘውን ቤቶቻችንን ካፈረሰች በኋላ ከፍርስራሽ መውጣት እንዳለብን እየተነገረን ነው፤ በልጆቻችን ውስጥ አንድ የደም ጠብታ እንኳ ቢቀር ጋዛን አንለቅም፣ ተስፋም አንቆርጥም” ብለዋል ነዋሪዎቹ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ወደ ዋይትሃውስ እንደገቡ የጋዛ ፍርስራሽ እስኪጸዳ ድረስ ፍልስጤማውያን እንደ ግብጽ እና ዮርዳኖስ ባሉ ሀገራት እንዲጠለሉ ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ዶናልድ ትራምፕ ጋዛን ለመቆጣጠር የያዙትን እቅድ በርካታ የዓለም ሀገራ በመቃወም ላይ ይገኛሉ።
የጋዛ ተፈናቃዮችን በቋሚነት እና በጊዜያዊነት እንዲያስጠልሉ ከትራምፕ ትእዛዝ የተሰጣቸው ግብጽ እና ዮርዳኖስ እቅዱን ውድቅ ያደረጉት ሲሆን፥ የፍልስጤም እና የአረብ መሪዎችም አጥብቀው ተቃውመውታል።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምት መደረሱን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍሊስጤማውያን ወደ ፈራረሰቸው መንደራው እየተመሙ ይገኛሉ።
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ከሆነ ከአጠቃላይ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል 1.9 ሚሊየን ወይም 90 በመቶው በ15 ወሩ ጦርት ከመኖሪያቸው ለመፈናቀል ተገደዋል።