ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ከዩክሬን አቻቸው ጋር በስልክ ተወያይተዋል
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣኢብ ኤርዶሃን ሩሲያና ዩክሬንን ለማደራደር በድጋሚ ጥያቄ አቀረቡ፡፡
ኤርዶሃን ጥያቄውን ያቀረቡት የዩክሬኑ አቻቸው ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
የሩሲያንና የዩክሬንን መሪዎች በአካል የማገናኘት ፍላጎት እንዳላቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጹ የሚደመጡት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣኢብ ኤርዶሃን፤ ሀገራቱ ወደ ተኩስ አቁም እንዲገቡና ሰብዓዊ እርዳታ ያለገደብ እንዲተላለፍ የጀመሩት የማደራደር ሂደት ውጤት እያሳየ መምጣቱ ይታወቃል፡፡
ቱርክ ባደረገችው ጥረት የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲተላለፍ መደረጉም አይዘነጋም፡፡
ይሁንና ደም አፋሳሹን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በዘላቂነት ለመፍታት የሀገራቱ መሪዎች ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት መምጣት ወሳኝ እንደሆነ ኤርዶሃን በጥብቅ የሚያምኑት ጉዳይ ነው፡፡
አዳዲስ ክስተቶች እያስተናገደና እየተወሳሰበ የመጣው የዩክሬን ጦርነት መፍትሄ ካልተበጀለት ከባድ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል በርካቶች ስጋታቸውን ያነሳሉ፡፡
በተለይም አሁን ላይ ወደ ዩክሬን እየጎረፈ ያለው የጦር መሳሪያ ሞስኮ የከፋ እርምጃዎች ለመውሰድ ሊያስገድዳት እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
በምዕራባውን ድርጊት የተበሳጨችው ሩሲያ የዩክሬን አጋሮች ከድርጊታቸው ካልተቆተቡ "ዩክሬን ሙሉ በሙሉ መጥፋቷ አይቀሬ ነው" ነው በማለት በማስጠንቀቅ ላይ ትገኛለች፡፡
የሩሲያ የደህንነት ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፤ ሩሲያ በዩክሬን ከተሸነፈች ያሏትን የኒውክሌር አረር እንደምትጠቀም በቅርቡ መዛታቸውም አይዘነጋም፡፡