የምዕራባውያን ታንኮች በዩክሬን ጦርነት የሚያመጡት አንዳች ለውጥ የለም - ሩሲያ
ሩሲያ፤ “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” በሚል የጀመረችው ጦርነት እንደከበዳት ይነገራል
ሞስኮ፤ የምዕራባውያን ተግባር "ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ የሚያጠፋ ነው" ብላለች
ምዕራባውያን ሀገራት ለዩክሬን ተጨማሪ ታንኮች ቢያቀርቡም በጦርነቱ የሚያመጡት አንዳች ለውጥ የለም ስትል ሩሲያ ገለጸች፡፡
በጦርነቱ ዩክሬን ታሸንፋለች የሚለው “የምዕራባውያን ስሌት የተሳሳተ ነው” ያለቸው ሩሲያ ውሎ አድሮ በውሳኔያቸው ይጸጸታሉም ብላለች፡፡
የክሬምሊን ባለስልጣናት ይህን ያሉት፤ ጀርመን በሚገኘው ራምስቴይን የአሜሪካ ወታደራዊ አየር መረፊያ የተሰባሰቡት የአውሮፓ መሪዎች ፤ ጀርመን ሰራሽ ሊዮፓርድ 2 ታንኮች ወደ ዩክሬን ለመላክ በርሊንን ለማሳመን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውንና በዚህም አወንታዊ ነገሮች መሰማታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "እንዲህ ያሉ አቅርቦቶች በመሰረቱ ምንም ነገር እንደማይቀይሩ ነገር ግን በዩክሬን እና በዩክሬን ህዝብ ላይ ችግር እንደሚፈጥር ደጋግመን ተናግረናል" ሲሉ ለጋዜጠኖች ተናግረዋል፡፡
ምዕራባውያን ዩክሬንን በጦር መሳሪያ ማገዛቸው ጦርነቱ እንዲባባስ አድርጎታል ያሉት ቃል አቀባዩ፤"በጦርነቱ የኔቶ ሀገራት ቀጥተኛ ተሳትፎ እያየን ነው”ም ብለዋል፡፡
ይሁን እንጅ መሰሰል የምዕራባውያን ተግባራት ከቀጠሉ "ዩክሬን ሙሉ በሙሉ መጥፋቷ አይቀሬ ነው" ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የውጥረቶች መባባስ ተከትሎ አሁን ላይ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ብላ በምትጠራውን የዩክሬን ጦርነት የተሟላ ድል ለመቀዳጀት የሀገሪቱን የደህንነት ምክር ቤትን ሰብስበው መወያየታቸውንም ተገልጿል፡፡
በደህንነት ምክር ቤቱ ስብሰባ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ ተገኝተዋልም ነው የተባለው፡፡
“ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” በሚል በወርሃ የካቲት 2021 ጦሯን ወደ ዩክሬን ምድር የላከችው ሩሲያ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ እንደከበዳት ይነገራል፡፡
በተለይም በቅርቡ በምዕራባውያን ሚታገዘው የዩክሬን ጦር በመልሶ ማጥቃት የወሰደው እርምጃ የሩሲያን ግስጋሴ ጥያቄ ውስጥ ከማስገባቱም በላይ የክሬምሊን ባለስልጣናትን “እንሸነፍ ይሆን?” ወደሚል ስጋት ውስጥ ከተተ ጉዳይ ሆኗል፡፡
የሩሲያ የደህንነት ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ፓቬል ኔድሜዴቭ ሩሲያ በዩክሬን ከተሸነፈች ያሏትን የኑክሌር አረር እንደምትጠቀም በቅርቡ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን የሚያስታጥቁትን የጦር መሳሪያ እንዲያቆሙ ያሳሰቡት ሜድቬዴቭ ሩሲያ ለዩክሬን በተሰጡት የጦር መሳሪያዎች ምክንያት ከተሸነፈች ግን የኑክሌር ጦርነት ይጀመራል ብለዋል፡፡