ቱርክ በዩክሬኑ የዛፖሪዝሂያ ኒውክሌር ጣቢያ ግጭት ጉዳይ ማሸማገል ትችላለች- ፕሬዘዳንት ኤርዶሃን
ኤርዶሃን፤ የቱርክን አሸማጋይ የመሆን ፍላጎት ለሩሲያው አቻቸው ፑቲን መናገራቸውም ተገልጿል
ቱርክ በጦርነት ውስጥ ካሉት ዩክሬንና ሩሲያ ጋር መልካም የሚባል ወዳጅነት እንዳላት ይታወቃል
ቱርክ በዩክሬኑ የዛፖሪዝሂያ ኒውክሌር ጣቢያ ግጭት ጉዳይ መሸምገል ትችላለች ሲሉ ፕሬዘዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ቱርክ የማሸማገል ሚናውን መጫወት እንደምትፈልግ ለሩሲያው አቻቻው ፑቲን እንዳሳወቁም ከቱርክ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት የተገኘ መረጃን ዋቢ በማድረግ ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ኤርዶሃን ቱርክ፤ ሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የዩክሬይንን የእህል ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ትልቅ ሚና እንደተጫወተች ሁሉ ፤አሁንም ትልቅ ሚና መጫወት ትችላለች ማለታቸውንም ተገልጿል፡፡
"ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ቱርክ በእህል ስምምነት ውስጥ እንዳደረጉት በዛፖሪዝሂያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ውስጥ የአመቻችነት ሚና መጫወት እንደምትችል ተናግረዋል" ነው ያለው ፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት፡፡
ባለፈው ወር ከዩክሬን አቻቸው ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጋር ለመነጋገር ወደ ኪቭ አቅንተው ነበሩት ኤርዶሃን፤ አሁን ላይ የዬክሬን-ሩሲያ የውጥረት ማዕከል የሆነውን የኒውክሌር ጣቢያ ጉዳይ ከባድ ጣጣ ሊስከትል የሚችል ጉዳይ መሆኑ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም፡፡
ኤርዶሃን በወቅቱ" ተጨንቀናል፤ ሌላ ቼርኖቤል (እንደፈረንጆቹ በሚያዚያ 26 ቀን 1986 የተከሰተ አስደንጋጭ የኒውክሌር አደጋ) አንፈልግም” ማለታቸውም ሚታወስ ነው፡፡
እናም አሁን በአውሮፓ ትልቁ በሂነው የዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ያለው ውጥረት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡
በቅረቡ ወደ ኒውክሌር ጣቢያው ያቀናውና በፋኤል ግሮሲ የሚመራው የተመድ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ቡድን ጣቢያው የዩክሬንና ሩሲያ ኃይሎች በሚያደርጉት ፍልሚያ ጥቃት እንደደረሰበት አስታውቋል፡፡
ለጥቃቱ ሞስኮና ኪቭ እር በርስ ከመወነጃጀል በዘለለ፤ እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ አካል አለመኖሩ እያነጋገረ ነው፡፡
ያም ሆኖ፤ በኒውከሌር ጣቢያው ላይ የከፋ ጥቃት ደርሶ በአውሮፓ ምድር ያልተፈለገ አደጋ ከማስከተሉ በፊት፤ ከሁለቱም ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነት እንዳለት የሚነገርላት ተርኪዬ አሸማጋይነቱ ሚና ለመጫወት እችላለሁ በማለት ላይ ናት፡፡
ቱርክ፤ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ለዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች በመስጠት እንዲሁም በምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በመቃወም ትታወቃለች፡፡