የቱርኩ ፕሬዝደንት ኢርዶጋን እስላማዊ ሀገራት ጸረ-እስራኤል ትብብር እንዲያደርጉ ጠየቁ
ኢርዶጋን ይህን ያሉት የቱርክ እና የፍልስጤም ባለስልጣናት የቱርክ እና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላት ሴት መገደሏን ከገለጹ በኋላ ነው
"የእስራኤልን ትዕቢት፣ ጥቃት እና መንግስታዊ ሽብር ማቆም የሚቻለው በእስላማዊ ሀገራት ጥምረት ነው" ሲሉ ኢርዶጋን ተናግረዋል
የቱርኩ ፕሬዝደንት ኢርዶጋን እስላማዊ ሀገራት ጸረ-እስራኤል ትብብር እንዲያደርጉ ጠየቁ ።
የቱርኩ ፕሬዝደንት ታይፕ ኢርዶጋን " እየጨመረ ያለውን የእስራኤል መስፋፋት ስጋት" ለመመከት እስላማዊ ሀገራት ጥምረት መፍጠር አለባቸው ብለዋል።
ኢርዶጋን ይህን ያሉት የቱርክ እና የፍልስጤም ባለስልጣናት ባለፈው አርብ በዌስትባንክ በተካሄደው እና የእስራኤልን መስፋፋት በሚያወግዘው ሰልፍ ላይ የቱርክ እና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላት ሴት መገደሏን ከገለጹ በኋላ ነው።
እስራኤል በአለምአቀፉ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት መከሰስ አለባት- የቱርኩ ኢርዶጋን
"የእስራኤልን ትዕቢት፣ ጥቃት እና መንግስታዊ ሽብር ማቆም የሚቻለው በእስላማዊ ሀገራት ጥምረት ነው" ሲሉ ኢርዶጋን በኢስታንቡል አቅራቢያ በተካሄደ የእስላማዊ ትምህርት ቤቶች ማህበር ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ ቱርክ ከግብጽ እና ሶሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል እርምጃዎችን የወሰደችው ለሊባኖስ እና ሶሪያ ጭምር ስጋት የሆነውን እየጨመረ የመጣውን የመስፋፋት ለመመከት የሚያሰችል አንድነት ለመፍጠር ነው ብለዋል። የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ባወጡት መግለጫ የኢርዶጋን መግለጫ "አደገኛ ውሸት እና ግጭት ቀስቃሽ" ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
ሚኒስትሩ የቱርክ መሪዎች እና የኢራን መሪዎች በቀጣናው ያሉ ለዘብተኛ የአረብ አስተዳደሮችን ደህንነት ለማናጋት ለአመታት ሲሰሩ ነበር ሲሉም ከሰዋል። ኢርዶጋን በቅርቡ የግብጹን ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲን አስተናግደው በጋዛ ጦርነት ጉዳይ እና በመካከላቸው የነበረውን የሻከረ ግንኙነት ለመጠገን በሚቻልበት ሁኔታ መክረዋል። በ12 አመታት ወዲህ የግብጽ ፕሬዝደንት ቱርክን ሲጎበኝ አል ሲሲ የመጀመሪያው ናቸው።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እየተሻሻለ የመጣው ቱርክ አረብ ኢምሬትስን እና ሳኡዲ አረቢያን ጨምሮ ከተቀናቃኞቿ ጋር ያለውን ውጥረት ለመፍታት ጥረት ማድረግ በጀመረችበት በ2020 ነበር። ኢርዶጋን እንዳሉት የሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከሶረያ ጋር ግንኙነቷን ያቋረጠችው ቱርክ ከሶሪያው ፕሬዝደንት በሽር አላሳድ ጋር "በየትኛውም ጊዜ" ንግግር ለማድረግ ግብዣ ታቀርባለች።
የእስራኤል ጦር ባለፈው አርብ እለት በቦታው በነበረው ተኩስ የውጭ ዜግነት ያላት ሴት ተገድላለች የሚለውን ሪፖርት እመረመረው እንደሆነ ገልጾ ነበር።
በጋዛ ጦርነት እያካሄደች ያለችውን እስራኤልን በሰብአዊ መብቶች ጥሰት የምትከሰው ቱርክ፣ ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ማቋረጧ ይታወሳል።