ኢርዶጋን አሜሪካ እና አውሮፓ በእስራኤል በቂ ጫና አላደረጉም ሲሉ ወቀሱ
ደቡብ አፍሪካ፣ እስራኤል በጋዛ የዘርማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች በማለት በአለምአቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ፊት አቁማታለች
ሀማስ በግብጽ እና በኳታር የቀረበውን የተኩስ አቁም እቅድ መቀበሉ ይታወሳል
ኢርዶጋን አሜሪካ እና አውሮፓ እስራኤል እንድትስማማ በቂ ጫና አላሳደሩም ሲሉ ወቀሱ።
የቱርኩ ፕሬዝደንት ታይፕ ኢርዶጋን ሀማስ የተኩስ አቁም እቅዱን ከተቀበለ በኋላ አሜሪካ እና አውሮፓ እስራኤል ተኩስ ለማቆም እንድትስማማ በቂ ጫና ሲያሳድሩ እንዳልነበረ ተናገሩ።
እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ያለውን ጥቃት የምታወግዘው ቱርክ ወደ ጋዛ አስቸኳይ እርዳታ እንዲገባ ጥሪ አቅርባለች። ቱርክ ምዕራባውያን ያለቅድመ ሁኔታ ለእስራኤል የሚያደርጉትን ድጋፍም ትኮንናለች።
አንካራ ከእስራኤል ጋር ስታደርገው የነበረውን የንግድ ልውውጥ ሙሉ በሙሉ ያቆመች ሲሆን አሁን ደግሞ ደቡብ አፍሪካ የወሰደችውን እርምጃ እንደምትቀላቀል ገልጻለች።
ደቡብ አፍሪካ፣ እስራኤል በጋዛ የዘርማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች በማለት በአለምአቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ፊት አቁማታለች።
እስራኤል የሚቀርብባትን የዘር ማጥፋት ክስ በጽኑ ትቃወማለች።
ኢርዶጋን በኢስታንቡል በተካሄደው የሙስሊም ምሁራን ስብሰባ ላይ ሀማስ፣ ግብጽ እና ኳታር ያቀረቡትን የተኩስ አቁም እቅድ ተቀብሏል፤ ነገርግን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጦርነቱ እንዲቆም አይፈልጉም ሲሉ ተናግረዋል።
"የኔታንያሁ መንግስት ፍላጎት በራፋ የሚገኙ ንጹሀንን ማጥቃት ነው" ያሉት ኢርዶጋን "አሁን ላይ ማን ሰላም እና ንግግር እንደሚፈልግ እና ማን ቀጣይነት ያለው ግጭት እንደሚፈልግ ግልጽ ሆኗል" ብለዋል።
አሜሪካም ሆነች አውሮፓ እስራኤል ተኩስ እንድታቆም ጫና ሲያደርጉባት አልታዩም ብለዋል።
የኢርዳጋን የደህንነት ኃላፊ የሆኑት ኢብራሂም ካሊን በተኩስ አቁም ጉዳይ እና እርዳታ በሚደርስበት ሁኔታ ከሀማስ መሪዎች ጋር እሁድ እለት በዶሃ መምከራቸውን ሮይተርስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
እስራኤል በጦርነቱ ሸሽተው የተጠለሉባትን ራፋን እንዳታጠቃ ጫና ቢደረግባትም፣ እስራኤል ማጥቃቷን ቀጥላበታለች።