ፑቲን ከወር በኋላ ቱርክን ሊጎበኙ እንደሚችሉ ኤርዶሃን ተናገሩ
ፕሬዝዳንት ፑቲን ቱርክ በምታስመርቀው የአኩዩ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ምርቃት ላይ ነው ሊታደሙ ይችላል የተባለው
በአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዛዣ የወጣባቸው ፕሬዝዳንት ፑቲን ቱርክ የአይሲሲ አባል ሀገር ባለመሆኗ በቁጥጥር ስር የመዋል ስጋት አይኖርባቸውም
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቱርክ ጉብኝት ሊያደርጉ እንደሚችሉ የቱርክ አቻቸው ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ገልጸዋል።
ፑቲን አንካራ በፈረንጆቹ ሚያዚያ 27 የአኩዩ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ጣቢያን ስታስመርቅ ሊገኙ እንደሚችሉ ነው ኤርዶሃን የተናገሩት።
የቱርክ የመጀመሪያው የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ በሩሲያው የኒዩክሌር ሃይል ኩባንያ ሮሳቶም የተገነባ መሆኑ ይታወቃል።
“ፑቲን በኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ጣቢያው ምርቃት ላይ የሚገኙበት እድል አለ፤ ካልሆነ ግን በበይነ መረብ በቀጥታ የምርቃቱ አካል ይሆናሉ” ብለዋል ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን።
ክሬምሊን ግን ቀደም ብሎ ፑቲን በምርቃት ስነስርአቱ ላይ ይገኛሉ በሚል ከቱርክ መገናኛ ብዙሃን የወጣውን መረጃ ማስተባበሉ ይታወሳል።
ሁለቱ መሪዎች የሀገራቱን የኢነርጂ ዘርፍ ትብብር የሚያሳድግ ምክክር በስልክ ማድረጋቸውን በመጥቀስ የፕሬዝዳንት ፑቲን ቱርክ የመገኘት ጉዳይ ሀሰት መሆኑን መግለጹንም የቱርኩ ኤቲቪ ዘግቧል።
በ20 ቢሊየን ዶላር ወጪ የተገነባው የአኩዩ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ጣቢያ 4 ሺህ 800 ሚጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል።
አራት የኒዩክሌር ማብለያዎች ያሉት የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ከወር በኋላ ወደ ስራ ይገባል ተብሏል።
ይህን የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ጣቢያ የገነባችው ሩሲያ ፕሬዝዳንት በምርቃት ስነስርአቱ ላይ የመገኘት ዜና መነጋገሪያ የሆነው የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በፑቲን ላይ ያወጣው የእስር ማዘዣ ነው።
ቱርክ የአይ ሲ ሲ አባል ሀገር አለመሆኗን የሚጠቅሰው የሬውተርስ ዘገባ፥ ክሬምሊን ፑቲን በአኩዩ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ምርቃት ላይ አይገኙም ያለበትን ምክንያት አልጠቀሰም ብሏል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን የአይሲሲ አባል በሆነችው ደቡብ አፍሪካ ለብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ይጓዛሉ ከተባለ ወዲህ የደቡብ አፍሪካ ፖለቲከኞች ለሁለት ተከፍለዋል።