የዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባል የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ፑቲንን የማሰር ግዴታ ውስጥ ገብታለች
ደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን አስራ ለዓለም አቀፉ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት እንድታስረክብ ተጠየቀች።
ዓለም አቀፉ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት ከቀናት በፊት በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል።
ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በሚል ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
ሩሲያ ፍርድ ቤቱ ረብ የለሽ እና የማይጠቅም ስትል ያጣጣለች ሲሆን ትእዛዙን ባስተላለፉ ዳኞች ላይ ክስ እንደምትመሰርት አስታውቃለች።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን የደቡብ አፍሪካ፣ ብራዚል፣ ቻይና፣ ሕንድ እና ሩሲያ ጥምረት የሆነው ብሪክስ የፊታችን ነሀሴ በፕሪቶሪያ ጉባኤውን ያካሂዳል።
በዚህ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍም የብሪክስ አባል የሆነችው ሩሲያን ወክለው ፕሬዝዳንት ፑቲን ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚመጡ ተገልጿል።
በፕሬዝዳንቱ ላይ የእስር ማዘዣ ያወጣው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ደቡብ አፍሪካ ህጉን እንድታከብር ጠይቋል።
ደቡብ አፍሪካ የፍርድ ቤቱ ፈራሚ ሀገር ስትሆን በዚህ ህግ መሰረት በፍርድ ቤቱ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች የማሰር እና አሳልፋ የመስጠት ግዴታ አለባት ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ደቡብ አፍሪካ በጉዳዩ ዙሪያ ከዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጋር እንደምትወያይ ገልጻለች። የደቡብ አፍሪካ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ናለንዲ ፓንደር እንዳሉት በጉዳዩ ዙሪያ ከሩሲያ ጋር እንደሚወያዩበት አስታውቀዋል።
እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ ሚኒስትሮች እና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚወያዩም ገልጸዋል።
ደቡብ አፍሪካ እና ሩሲያ ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ ከአንድ ወር በፊት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸው ይታወሳል።