ናይጄሪያ እና ቱርክ በስምንት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
ሁለቱ አገራት በጋራ ለመስራት ከተስማሙባቸው አጀንዳዎች መካከል የማእድን ልማት እና የመከላከያ ስምምነቶች ዋነኞቹ ናቸው
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በናይጄሪያ የሁለት ቀናት ጉብኝት ላይ ናቸው
ናይጄሪያ እና ቱርክ በስምንት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ፡፡
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በናይጄሪያ የሁለት ቀናት ጉብኝት ላይ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ከናይጄሪያ አቻቸው ጋር በሁለትዮሽ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል፡፡
ሁለቱ አገራት ከውይይታቸው በኋላ በስምንት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የተስማሙ ሲሆን ሀይል ልማት፣መከላከያ ኢንዱስትሪን ማዘመን ፤ማእድን ማውጣት እና አየር ንብረት ሁለቱ አገራት በጋራ ለመስራት ከተስማሙባቸው አጀንዳዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን በአፍሪካ ጉብኝታቸው ከናይጄሪያ በተጨማሪ አንጎላ እና ቶጎን እንደሚጎበኙ ዘገባው አክሏል፡፡
ፕሬዝዳንት ሙሀመዶ ቡሀሪ ከስምምነቱ በኃላ እንዳሉት ከቱርክ አቻቸው ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው ስምምነቶቹ የሁለቱን አገራት ግንኙነት እንደሚያሳድጉት ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን በበኩላቸው ሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደደረሰ ገልጸው በቀጣይ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር የማሳደግ አቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ቱርክ በአፍሪካ ካሉ 55 አገራት መካከል በ43ቱ አገራት ኢምባሲዎቿን መክፈቷ ለቱርክ-አፍሪካ ግንኙነት ትኩረት መስጠቷን ፕሬዝዳንቱ አክለዋል፡፡