ታሊባን የካቡል አየር ማረፊያን እንዲያስተዳድሩለት ከኳታር እና ቱርክ ጋር እየተነጋገረ ነው ተባለ
ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው አምስቱ ቋሚ የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሃገራት በዚሁ ጉዳይ ላይ ዛሬ እንደሚሰበሰቡ ይጠበቃል
ከአሁን በኋላ ከካቡል የሚደረጉ በረራዎች የክፍያ ብቻ ናቸው ተብሏል
የአሜሪካ ጦር ሙሉ በሙሉ አፍጋኒስታንን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ሃገሪቱን የተቆጣጠረው ታሊባን የካቡል አየር ማረፊያን እንዲያስተዳድሩለት ከኳታር እና ቱርክ ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ፈረንሳይ አስታወቀች፡፡
ታሊባን አየር ማረፊያውን በተመለከተ ከኳታር እና ቱርክ ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ያስታወቁት የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዢን ዬቭስ ለ ድሬይን “ከአሁን በኋላ አፍጋኒስታንን ለቀው ለመውጣት የሚፈልጉ ሁሉ ሊወጡ የሚችሉት በንግድ (የክፍያ) በረራዎች ብቻ” እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ለድሬይን “ኢንፎ ፍራንስ 2” ከተባለው የሃገራቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸው “የአየር ማረፊያውን ደህንነት አስመልክቶ (የተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ መከበር አለበት፡፡ ስለ አየር ማረፊያው አስተዳደር ከኳታር እና ከቱርክ ጋር እየተወያዩ ነው። በአውሮፕላን ማረፊያው የሚኖረው ተደራሽነት የተጠበቀ እንዲሆን መጠየቅ አለብን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሃገራቸው በታሊባን ላይ ጫና ማድረጓን እንደምትቀጥል ነገር ግን እንደማትደራደር ነው ለድሬይን የተናገሩት፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት አሁንም ከአፍጋኒስታን መውጣት ለሚፈልጉ ዜጎች ደህንቱ የተጠበቀ የበረራ ከባቢን "safe zone" በካቡል እንዲያመቻች ፈረንሣይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ጠይቀዋል፡፡
ፈረንሳይን ጨምሮ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው አምስቱ ቋሚ የምክር ቤቱ አባል ሃገራት ማለትም ብሪታኒያ፣ አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቻይና በዚሁ ጉዳይ ላይ ዛሬ እንደሚሰበሰቡ ይጠበቃል፡፡
ዜጎችን ከአፍጋኒስታን ለማውጣት ሲደረግ የነበረው ጥረት ቀነ ገደቡ መጠናቀቁን ተከትሎ መቆሙ ይታወሳል፡፡
አሜሪካ ላለፉት 20 ዓመታት የነበራትን የአፍጋኒስታን ቆይታ አጠናቃ ሙሉ በሙሉ መውጠቱን ተከትሎ ታሊባን “አፍጋኒስታን አሁን ነጻ እና ሉዓላዊ ሀገር ነች” ሲል ማወጁም የሚታወስ ነው፡፡