ቱርክ ፍስጤማውንን ለመታደግ ወታደራዊ ጣልቃገብነት ልታደርግ እንደምትችል አስጠነቀቀች
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣብ ኢርዶጋን እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ለመግታት ጠንካራ መሆን አለብን ብለዋል
እስራኤል በሰጠችው ምላሽ ፕሬዝዳንቱን ከሳዳም ሁሴን ጋር አመሳስላቸዋለች
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኢርዶጋን በፍልስጤማውያን ላይ እስራኤል እያደረሰች የምትገኝውን ጥቃት ለመከላከል ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ሊደረግ እንደሚችል አስጠነቀቁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ በትላንትናው አለት ፓርቲያቸው ኤኬፒ በነበረው ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር በሊቢያ እና በአዘርባጃን ወታደሮቻችንን እንደላክነው በጋዛም ተመሳሳዩን እናደርጋለን ሲሉ ዝተዋል፡፡
የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የቃላት ጦርነት የጨመረ ሲሆን ከዚህ ባለፈም አንካራ ከቴልአቪቭ ጋር የምታደርገውን የንግድ ግንኙነት ለማቋረጥ በቅርቡ ውሳኔ ላይ መድረሷ ይታወሳል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣብ ኤርዶሀን በትላንትናው ንግግራቸው እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ለመግታት ጠንካራ መሆን አለብን ብለዋል፡፡
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እስራኤል ካትዝ ለዚህ በሰጡት ምላሽ “የቱርኩ ፕሬዝዳንት የቀድሞውን የኢራቅ አምባገነን መሪ ሳዳም ሁሴን አካሄድን እየተከተሉ ነው፤ በኢራቅ ምን እንደተፈጠረ እና እንዴት እንደተጠናቀቀ ለፕሬዝዳንቱ አስታውሷቸው” የሚል ጽሁፍ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መስርያ ቤት በበኩሉ “የዘር ጨፍጫፊው አዶልፍ ሂትለር እንዳበቃለት ሁሉ የእስራኤሉም ጠቅላይ ሚንስትር ያበቃላቸዋል” ሲል ለእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጽሁፍ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
አክሎም “ናዚ ላደረሰው ጭፍጨፋ ተጠያቂ እንደነበር ሁሉ የእስራኤል አስተዳደርም በተመሳሳይ ተጠያቂ ነው ሰብአዊ የሆነ በሙሉ ከፍልስጤማውያን ጎን ቆሟል፤ ፍልስጤምን እንድታጠፉ አንፈቅድላችሁም” ነው ያለው።
በትላንትናው እለት በጎላን ተራሮች በእግርኳስ ሜዳ ላይ ሂዝቦላ ፈጽሞታል በተባለ ጥቃት የ12 ህጻናት እና ታዳጊ እስራኤላውያን ህይወት ማለፉን ተከትሎ እስራኤል በሊባኖስ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች፡፡
ሂዝቦላ ምንም እንኳን በትላንቱ ጥቃት እጁ እንደሌለበት ቢያሳውቅም እስራኤል ትላንት እና ዛሬ በአጻፋ ምላሹ ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ ቡድኑ በሀገሪቱ ሰሜናዊ ድንበር አቅራቢያ የሮኬት ጥቃት ስለማድረሱ እየተነገረ ነው፡፡
በሂዝቦላ እና በእስራኤል መካከል ያለው ውጥረት ወደለየለት ጦርነት አምርቶ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ተጨማሪ ቀውስን እንዳያስከትል እየተሰጋ በሚገኝበት ጊዜ ቱርክ የሰነዘረችው ዛቻ ተጨማሪ ስጋትን ስለመፍጠሩ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡