የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች ክርስቲያኖችን ይቅርታ ጠየቁ
አዘጋጆቹ ከእየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው እራት ታሪክ ጋር በተያያዘ ባስተላለፉት መልዕክት ነው ይቅርታ የጠየቁት
በመከፍቻው ላይ የታየውን ትዕይን ተከትሎ የተቆጡት የእምነቱ ተከታዮች አዘጋጁ ይቅርታ እንዲጠይቅ ተጽእኖ ሲያደርጉ ሰንብተዋል
የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች የለዮናርዶ ዳቬንቺን የእየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው እራት ስዕልን ተጠቅመው ላስተላለፉት መልእክት ይቅርታ ጠየቁ፡፡
እየሱስ ክርስቶስ ከሀዋሪያቶቹ ጋር ያሳለፈው የመጨረሻው እራት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የሀይማኖቱ መሰረት ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል የተፈጸሙበት ሲሆን ሊዮናርዶ ዳቬንችም ይህን የሚወከል ታዋቂ ስእል ለአለም አበርክቷል፡፡
ባሳለፍነው አርብ የተካሄደው የፓሪሱ ኦሎምፒክ መክፈቻ በርካታ አድናቆቶች ቢቸሩትም በዛው ልክ ተቃውሞ እና መነጋገርያ የነበሩ ሁነቶችም ነበሩበት፡፡
አዘጋጆቹ የስዕሉን አቀመማጥ በመጠቀም ታሪኩን የግሪክ አማልክት እና ከሌሎች ከሀይማኖቱ ጋር የማይገናኙ ውክልናዎችን ለማንጸባረቅ ተጠቅመውበታል፡፡
ይህን ተከትሎ በርካታ ተከታዮች እንዳለው የሚነገርለት የካቶሊክ እምነት ተከታዮችን ጨምሮ የክርስትና አማኞች በመክፈቻው ላይ በተላለፈው መልዕክት ቁጣቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
የፈረንሳይ ፣ የግሪክ ፣ የሩሲያ እና የግብጽ ታላላቅ የክርስትና እምነት መሪዎች ድርጊቱ መላው ክርስቲያንን በላተገባ መንገድ የገለጸ እና ለሀይማኖቱም ተገቢውን ክብር ያልሰጠ አሳፋሪ ድጊት ነው ሲሉ አውግዘውታል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም አዘጋጅ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ እና ይቅርታ እንዲጠይቅ በርካቶች ግፊት ሲያደርጉ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አዘጋጆቹ በመጀመርያዎቹ ቀናት የቀረበባቸውን ትችት የነጻነት ሀገር መሆናችንን የሚያሳይ መልዕክት ያስተላለፍንበት ነው በማለት ለማስተባበል ቢሞክሩም የተቃውሞዎች መበረከትን ተከትሎ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ቃል አቀባይ አን ዴካምፕስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በመክፈቻው ላይ በታየው ትርኢት የግሪክን አማልክት የሚወክሉት ደስታን እና ክብረ በአልን የሚያንጸባርቁ ናቸው ብለዋል፡፡
በዚህ ማስተላለፍ የፈለግነው ደስታን ፣ መቻቻለን እና አብሮ መኖርን እንጂ ድርጊቱ በሀይማኖት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ታስቦ የተደረገ አይደለም በዚህም ያስከፋነው አካል ካለ ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል።