የኬንያ መንግስት የታክስ ማሻሻያዎች የልማት ሰራዎችን ለመሰራት እና የሀገሪቱን ብድር ለመቀነስ አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል
የኬንያ መንግስት ተጨማሪ ታክሶችን በመጣል ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ያስችለኛል ያለው ህግ በኬንያ ወጣቶች ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል።
ፋይናንሻል ቢል ምንድነው?
የፋይናስ ቢል ሁልጊዜ አዲሱ የፊሲካል አመት ከመጀመሩ በፊት ከሰኔ እስከ ከሐምሌ ባለው ጊዜ ለፓርላማው የሚቀርብ ረቂቅ ህግ ነው።
የኬንያ መንግስት 2024/25 ባቀረበው ረቂቅ የታክስ ህግ፣ የበጀት ጉድለት ለመምሙላት እና ብድር ለመቀነስ ከታክስ በተጨማሪ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ አልሟል።
የኬንያ ብድር ከሀገሪቱ አጠቃላይ ገቢ ጋር ሲነጻጸር 68 በመቶ ሲሆን የዓለም ባንክ እና ኢንተናሽናል ሞናተሪ ፈንድ(አይኤምኤፍ) እንዲሆን ከሚጠብቁት 55 በመቶ ከፍ ያለ ነው።
የኑሮ ውድነትን ይጨምራል፤ የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ያናጋል የሚሉት ተቃዋሚዎች፣ የኬንያ መንግስት ያስበውን የታክስ ጭማሪ እንዲተወው ጠይቀዋል።
በኬንያ የፋይናስ ቢል ተቃውሞ ሲገጥመው ይህ የመጀመሪ አይደለም።
በፈረንጆች 2022 ሲመረጥ የድሀዎችን ህይወት ለማሻሻል ቃል የገባው የፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ አስተዳደር፣ ባለፈው አመት ባቀረበው ሀውሲንግ ታክስም ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።
በአዲሱ ህግ በእቅድ ተይዘው የነበሩ የታክስ ማሻሻያ እርምጃዎች
ተቃውሞ ያስነሳው አዲሱ ህግ ዳቦ፣ አትክልት ዘይት እና ስኳርን ጨምሮ በመሰረታዊ ፍላጎቶች ላይ ታክስ የሚጨምር እና የሞተር ተሽከርካሪ ባለቤቶች በአመት የተሽከርካሪውን ዋጋ 2.5 በመቶ በአመት እንዲከፍሉ የሚያደርግ ነው።
ሌላው "ኢኮ ታክስ" የተባለው ፎጣዎችን እና ዳይፐሮችን ጨምሮ በንጽህና መጠበቂያዎች ላይ የተጣለው ታክስም የተቃውሞ ምንጭ ሆኗል።
አዲሱ ህግ፣ ከአዳዲሶቹ ታክሶች በተጨማሪ አሁን ባለው የፋይናንስ ግብይት ታክስ ላይ ጭማሪ ለማድረግ አስቧል።
የኬንያ መንግስት የታክስ ማሻሻያዎች የልማት ሰራዎችን ለመሰራት እና የሀገሪቱን ብድር ለመቀነስ አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት መንግስት በመኪና ባለቤትነት፣ በዳቦ እና በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ የታሰበውን የኢኮ ታከስ ጨምሮ የተወሰኑትን ለመሰረዝ የአቋም መለሳለስ አሳይቶ ነበር።
የሀገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስተር መንግስት ያቀደውን ታክስ የማይሰበስብ ከሆነ በ2024/25 የበጀት አመት 1.56 ቢሊዮን ዶላር ክፈጉድለት እንደሚፈጥር ተናግሯል።
ተቃውሞውን ተከትሎ መንግስት የታክስ ህጉን በድጋሚ እንደሚያየው እና እንደሚያሻሽለው ቢገልጽም ተቃውሞው ሊበርድ አልቻለም።
በትናንትናው እለት ወደ ሀገሪቱ ፓርላማ በኃይል ጥሰው በገቡ ተቃዋሚዎች እና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።