በኬንያው ተቃውሞ የኦባማ እህት በአስለቃሽ ጭስ ተመታች
አውማ ኦባማ በአስለቃሽ ጭስ የተመታችው በኬንያ ፓርላማ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት ነው ተብሏል
የታክስ ማሻሻያውን የተቃወሙት ወጣቶች ወደ ፓርላማ በኃይል ጥሰው ለመግባት በሞከሩበት ወቅት ቢያንስ አምስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሌሎች በርካቶች ቆስለዋል
በኬንያው ተቃውሞ የኦባማ እህት በአስለቃሽ ጭስ ተመታች።
በኬንያ ፓርላማ ደጃፍ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፈችው በአንድ ወገን የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ እህት ኬንያዊቷ አክቲቪስት አውማ ኦባማ በአስለቃሽ ጭስ ከተመቱት መካከል መሆኗ ተገልጿል።
የኬንያ ፓርላማ የታክስ ማሻሻያውን ማጽደቁን የተቃወሙት ወጣቶች ወደ ፓርላማ በኃይል ጥሰው ለመግባት በሞከሩበት ወቅት ቢያንስ አምስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሌሎች በርካቶች መቁሰላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
አውማ ኦባማ ለምን በዚያ እንደተገኘች በሲኤንኤን ስትጠየቅ መታየቷን ዘገባው ጠቅሷል።
"እኔ እዚህ ያለሁት... ምን እየሆነ እንዳለ ተመልከት። ወጣት ኬንያዊውን ለመብታቸው ሰልፍ ወጥተዋል። መፈክር እና ሰንደቅአላማ ይዘው ነው የወጡት። ሌላ ማየት አልቻልኩም" ስትል ተናግራለች።
ከኦውማ ጀርባ ቆሞ የነበረው ግለሰብ ደግሞ "ቅኝ ግዛት በኬንያ አላበቃም" የሚል መፈክር ተሸክሞ ይታያል። ሌላኛው ደግሞ "ይህ ሀገራችን ነው።" እያለ ሲጮህ ይሰማል።
አውማ ኦባማ በተቃውሞ ሰልፉ መሳተፏን የሚያሳይ ፎቶ በኤክስ ገጿ ቀደም ብላ ለጥፋ ነበር።
የቀድሞ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ቢሮ በኦውማ ኦባማም ይሁን በኬንያ ብጥብጥ ገዳይ ወዲያውኑ አስተያየት መስጠት እንደማይችል መግለጹን ዘገባው ጠቅሷል።
የኬንያ መንግስት ተጨማሪ ታክሶችን በመጣል ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ያስችለኛል ያለው ህግ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።
ተቃውሞ ያስነሳው አዲሱ ህግ ዳቦ፣ አትክልት ዘይት እና ስኳርን ጨምሮ በመሰረታዊ ፍላጎቶች ላይ ታክስ የሚጨምር እና የሞተር ተሽከርካሪ ባለቤቶች በአመት የተሽከርካሪውን ዋጋ 2.5 በመቶ በአመት እንዲከፍሉ የሚያደርግ ነው።
ሌላው "ኢኮ ታክስ" የተባለው ፎጣዎችን እና ዳይፐሮችን ጨምሮ በንጽህና መጠበቂያዎች ላይ የተጣለው ታክስም የተቃውሞ ምንጭ ሆኗል።
አዲሱ ህግ፣ ከአዳዲሶቹ ታክሶች በተጨማሪ አሁን ባለው የፋይናንስ ግብይት ታክስ ላይ ጭማሪ ለማድረግ አስቧል።
የኬንያ መንግስት የታክስ ማሻሻያዎች የልማት ስራዎችን ለመሰራት እና የሀገሪቱን ብድር ለመቀነስ አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።