ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማቆም ሃማስን ከማጠናከር ውጭ ፋይዳ የለውም - ካሜሮን
የብሪታንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀገራቸው ለእስራኤል የምትሸጠው የጦር መሳሪያ ከአሜሪካ አንጻር እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል
ብሪታንያ ከ2015 ጀምሮ ለእስራኤል 1 ቢሊየን ፓውንድ የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን መሸጧ ተገልጿል
ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማቆም “ትክክለኛው መንገድ አይደለም” አሉ የብሪታንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን።
እርምጃው ሃማስን ከማጠናከር ውጭ ፋይዳ የለውም ማለታቸውም ተዘግቧል።
እስራኤል በራፋህ የእግረኛ ጦሯን አስገብታ ወረራ ከፈጸመች አሜሪካ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ለማቆም ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም ብሪታንያ የአሜሪካን ፈለግ ልትከተል ትችላለች ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ካሜሮን፥ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ በመሸጥ ሁለቱ ሀገራት ለንጽጽር የሚቀርቡ አይደሉም ብለዋል።
እስራኤል ከውጭ ከምታስገባቸው የጦር መሳሪያዎች የብሪታንያ ድርሻ 1 በመቶ ብቻ ነው።
ይሁን እንጂ እስራኤል አለማቀፍ የሰብአዊ ህግን ከጣሰች ለንደን ሽያጯን ልታቋርጥ ትችላለች ብለዋል ሚኒስትሩ።
የተቃዋሚ ፓርቲው ሌበር እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ለንደን የዋሽንግተንን አቋም እንድትይዝ ግፊት እያደረጉ መሆኑን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ብሪታንያ ከፈረንጆቹ 2015 ወዲህ ለእስራኤል 1 ቢሊየን ፓውንድ የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎች እንደሸጠች መረጃዎች ያሳያሉ።
“ቢኤኢ” የተባለው የብሪታንያ ኩባንያ እስራኤል ለምትጠቀምባቸው ኤፍ-35 የጦር አውሮፕላኖች 15 በመቶ ግብአቶችን ያቀርባል።
የኔታንያሁ አስተዳደር እነዚህን የጦር ጄቶች በራፋህ ጥቃት ለመፈጸም እየተጠቀመባቸው ንጹሃን እየተገደሉ ነው የሚሉ የመብት ተሟጋቾች ኩባንያው ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን እንዲያቋርጥ እየጠየቁ ነው።
የራፋሁ ዘመቻ ከአጋሯ አሜሪካ ጀምሮ በተለያዩ ሀገራትና አለማቀፍ ተቋማት ተቃውሞ እየደረሰባት ያለችው እስራኤል ግን በከተማዋ የመሸጉ ታጣቂዎችን ካልደመሰስኩ የጋዛ ጦርነት ድልን አላውጅም ብላለች።